አርባምንጮች ከወራጅ ቀጠና ለመዉጣት አዳማ ከተማዎች በበኩላቸዉ ደረጃቸዉን ከፍ ለማድረግ ወደ ሜዳ የገቡበት ጨዋታ ካለምንም ጎል በአቻ ዉጤት ተጠናቋል።
ሁለቱም ቡድኖች የማሸነፍ ወኔን ይዘዉ በፈጣን እንቅስቃሴ ጨዋታቸዉን የጀመሩ ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የማጥቃት እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን የግብ እድሎችን ለመፍጠር ሙከራዎችን አድርገዋል።
ለአብነትም በአርባምንጮች በኩል ተመስገን ደረስ እና በአዳማ በኩል ደግሞ ቦና ዐሊ የግብ ክልል ዉስጥ ደርሰዉ ያመከኗቸዉ ለግብ የሚሆኑ ኳሶች ተጠቃሽ ናቸዉ።
- ማሰታውቂያ -
በመጀመሪያዉ አጋማሽ ሁለቱም ቡድኖች ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን የአርባንጮ ለጎል የቀረቡ እንቅስቃሴዎች የተሻሉ ነበር።
አዞዎቹ መሪ ሊሆኑ የሚችሉበት አጋጣሚን አቡበከር ሻሚ ሊፈጥር የነበረ ቢሆንም የግቡ አግዳሚ የመለሰበት ኳስ በአርባምጮች በኩል የሚያስቆጭ ሆኖ ነበር ያለፈዉ።
ከዚህ በኋላ በሁለቱም ክለብ በኩል ብዙም አጥጋቢ የሚባል እንቅስቃሴ ሳይደረግ የመጀመሪያዉ አጋማሽ ያለ ግብ 0-0 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
በሁለተኛዉ አጋማሽ አዳማ ከተማዎች የጎል እድል ለመፍጠር የአጥቂ ስፍራዉን ሊያጠናክሩለት የሚችሉ ተጫዋቾችን ቀይሮ ይዞ ቢገባም በዉጤቱ ላይ ግን ለዉጥ ሊመጣ አልቻለም። በአርባምንጮች ረገድም እንደመጀመሪያው አጋማሽ ጥሩ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ በሁለተኛዉ አጋማሽ ሊደረግ አልቻለም።
በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች አዳማ ከተማዎች በተደጋጋሚ ወደ አዞዎቹ የግብ ክልል መድረስ የቻሉ ቢሆንም ነገር ግን ያገኟቸዉን እድሎች ወደ ግብ ሳይቀይሩ ሁለተኛዉ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ግዜም 0-0 በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
አርባምንጭ ከተማዎች አሁንም ከወራጅ ቀጠናዉ መዉጣት ሳይችሉ በ26 ነጥብ የደረጃዉ ግርጌ 14ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ አዳማ ከተማዎች በበኩላቸዉ የነበራቸዉ 32 ነጥብ ላይ አንድ በመጨመር በ33 ነጥብ ከሀዲያ ሆሳዕና እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር ነጥቡን እኩል ማድረግ ችሏል።