የ2015 የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአመቱ ወጣት ኮከብ ተጨዋች ተብሎ የተመረጠው ዮሴፍ ታረቀኝ በግብጹ አረብ ኮንትራክተር የሙከራ ዕድል ተሰጥቶት ዛሬ ለሊት 11 ሰአት ወደ ካይሮ ያቀናል።
ተጨዋቹ በግብጹ ክለብ ለስድስት ቀናት የሙከራ እድል የተሰጠው ሲሆን ሙከራውን በስኬት ካጠናቀቀ ከአዳማ ከተማ ጋር ቀሪ የ3 አመት ውል ስላለው ሁለቱ ክለቦች ለድርድር የሚቀመጡ ይሆናል። ተጨዋቹ እንደገለጸው “ያገኘሁትን ዕድል ለመጠቀም ከእግዚአብሄር ጋር የምችለውን ሁሉ አደርጋለሁ” ብሏል። ዮሴፍ ታረቀኝ የአመቱ ኮከብ ወጣት ተጨዋች ተብሎ በተመረጠ በአምስት ቀናት ልዩነት ይህን እድል ማግኘቱ ታውቋል።
35 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለውና ኦስማን አህመድ ኦስማን የተሰኘ ስታዲየም ባለቤት የሆነው አረብ ኮንትራክተር ክለብ /አልሞካውሉን አል አረብ / መቀመጫው ግብጽ መዲና ካይሮ ውስጥ ሲሆን አልአህሊ ሻምፒዮን በሆነበት የግብጽ ፕሪሚየር ሊግ በ44 ነጥብ 7ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።