ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 ስድስት የ28ኛ ሳምንት እና አንድ የ26ኛ ሳምንት ተስተካካይ ጨዋታ በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም ተደርጎ አራት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 22 ጎሎች በ17 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብም 18 በጨዋታ አራት በፍፁም ቅጣት ምት ነው። በሳምንቱ 26 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ ተጫዋች ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ሰኞ ሰኔ 5 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች አስናቀ ተስፋዬ (ለገጣፎ ለገዳዲ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያሰጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድ፥ ተስፋዬ አለባቸው(መቻል) እና በኃይሉ ግርማ (መቻል) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ፥ አብነት ደምሴ (ኢትዮ ኤሌትሪክ) እና ፍቅረየሱስ ተ/ብርሀን (ሀድያ ሆሳዕና) በተለያዩ 10 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 2 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 2000 /ሁለት ሺ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ ጋር ባደረገው የ26ኛ ሳምንት እግር ኳስ ጨዋታ የቅዱስ ጊዬርጊስ ክለብ ደጋፊዎች አወዳዳሪ አካልንና ግለሰብን(የሚዲያ ባለሞያን) አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ቀርቦ የክለቡ ደጋፊዎች በዕለቱ ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ጥፋት አጥፍተው ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 75000/ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ወስኗል።