*….ዕገታው ከአውቶቡስ ወደ አሰልጣኞች ዞሯል…
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዝናብ ምክንያት ሙሉ በሙሉ መቋረጡ ከተወሰነ በኋላ ቡድኖቹ ከድሬዳዋ ወደ የከተሞቻቸው እየተመለሱ ነው።
የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ወይስ መቆራረጥ የበዛበት ፕሪሚየር ሊግ ነው የተባለለት ሊጉ ከዋሊያዎቹ የጊኒ የደርሶ መልስ ጨዋታ በኋላ ሲጀመር በተስተካካይ ይካሄድ ተብሎ በመወሰኑ ሁሉም ክለቦች ወደየመጡበት ሲመለሱ የአዳማ ከተማ አሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለና የኢትዮ ኤሌክትሪኩ አሰልጣኝ ገዛኧኝ ከተማ ግን ሳይመለሱ ቀርተዋል።
ከታማኝ ምንጭ በተገኘ መረጃ ሁለቱ አሰልጣኞች ክለቦቻቸው በነበሩበት ሆቴል የተጠቀሙበትን ሂሳብ መክፈል ባለመቻላቸው በተያዥነት ድሬዳዋ መቅረታቸው ታውቋል። አዳማ ከተማ ውጤታማ ጉዞ እያደረገ ባለበት ሂደት አሰልጣኙ ያለ ሀላፊነቱ ይህን መሰል የሞራል ጉዳት ደርሶበት ውጤት ቢጠፋ አመራሮቹ ሊያሰናብቱት ይደፍሩ ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ሆኗል። በወጣቶቹ ላይ ዕምነት ጥሎ ዮሴፍ ታረቀኝን ለዋሊያዎቹ የመመረጥ ዕድል የፈጠረው አሰልጣኝ ይታገሱ የክለቡ ማናጅመንትና የፋይናንስ ክፍልን ሃላፊነት በጫንቃው ላይ እንዲሸከም መደረጉም የታሪካዊ ክለቡ ስም ላይ ጥላሸት የቀባ ሆኗል።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮ ኤሌክትሪክም ላረፈበት ሆቴል ሙለ ክፍያ አለመፈጸሙና አሰልጣኝ ገዛኧኝ ኸልዴ መታገቱ ከገንዘብ ዕጥረት ሳይሆን ከዝርክርክ አሰራር የመነጨ ሳይሆን እንደማይቀር የብዙዎች ግምት ሆኗል። ቡድኑ በአውሮፕላን ቲኬት ክፍያ ላይ በተፈጠረ ልዩነት ቀን ሊነሱ የነበረው ቀርቶ ማምሻውን ሊመለሱ መሆኑን እንደማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ሁለቱ ታሪካዊና የበርካታ ስፖርት አፍቃሪ ተወዳጅ ክለቦች የአመራር ድክመት አሰልጣኞቻቸው በሆቴል ክፍያ መታገታቸውና ከአውቶቢስ ዕገታ ወደ አሰልጣኝ ዕገታ መዛወሩ እግርኳሳችን ላይ ምን እየተካሄደ ነው ..? ኳሱስ የሚመራው በነማን ነው ..? የሚል ጥያቄም አስነስቷል።
ሁለቱ አሰልጣኞች መቼ ወደ አዲስ አበባና አዳማ ከተማ ይመለሳሉ የሚለው ጥያቄ ምላሽ የሚያገኘው ግን በክለቦቻቸው ፈጣን የክፍያ ምላሽ ብቻ ይሆናል።