” ውጤቱን በጸጋ እቀበላለሁ ምክንያቱም
ከግለሰብ ሀገር ይበልጣል’
አቶ ኢሳያስ ጅራ
የኢት.እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት
👉”የፌዴሬሽኑ ጠቅላላ ጉባኤ አባላት በያዙት ካርድ የሚመርጥ እንጂ የሆነ ሰው በሚፈጥረው ጫና የማይፈልገውን ይመርጣል ብዬ አላምንም” ሲሉ ፕሬዝዳንታዊው ዕጩ ፕሬዝዳንት ኢሳያስ ጅራ ተናገሩ።
ፌዴሬሽኑን ባለፉት አራት አመታት በፕፔዝዳንትነት የመሩትና ከሶስቱ ተወዳዳሪዎች መሃል አንዱ የሆኑት አቶ ኢሳያስ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡተ መግለጫ “በጠቅላላ ጉባኤው 126 ድምጽ ሰጪዎች አሉ ለጉባኤው ክብር ይኑረን በምርጫ ኮዱ በአካሄዱ ለሌሎቹ ፌዴሬሽኖች ምሳሌ መሆን ይችላል ውጫዊ ጫና ለውጥ ይኖረዋል ብዬ አላስብም” ሲሉ ተናግረዋል።
“ከአራት የአመራርነት ዘመኔ ሶስቱ አመታት የተሻለ ስራ የተሰራበት ነው” ያሉት አቶ ኢሳያስ ጅራ “በካፍ አካዳሚ ውስጥ በእጃችን የሆነ ሶስት ሜዳ የሚያሰሩ መሬቶች አሉ በቀጣይ ብመረጥ ይሄን ትልቅ ስራ ሰርቼ ለሀገሬ ሜዳ አበርክቼ የምኮራበት ስራ እንደምሰራ ተስፋ አደርጋለሁ ስልጠናን በተመለከተ ዲ ላይሰንስ እየተሰጠን ነው ሲ ላይሰንስን ካፍ ፈቅዶልናል ቢ እና ፕሮ ላይሰንስን ለማስጀመር ከካፍ ጋር እየተነጋገርን ነው በቀጣይ አመታት ይህን አጠናክረን የተሻለ የማብቃት ስራ እንሰራለን ብዬ አምናለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።
- ማሰታውቂያ -
“ባለፉት አመታት ስራዎች ባቀድናቸው ጊዜ ውስጥም በምንፈልገው መንገድ ያለመፈጸሙም በአገራዊ ለውጡና የኮሮና ወረርሽኝ እንዲሁሞ በተፈጠረው ችግር ክለቦች በመንግስት የሚደገፉ በመሆናቸው የሚፈጸሙ ሪፎርሞች ልናሳካቸው አልቻልንም
ከሊግ ኩባንያ ክለቦች ጋር ባለን የመልካም የስራ ግንኙነት በመጠቀም ክለቦች ገንዘብ ስለሚያገኙ አስገዳጅ ህጎችን በማውጣት የተሻለ ስራ ልንሰራ ሞክረናል ። በሻምፒየንስ ሊግና በኮንፌዴሬሽን ካፕ የሚካፈሉ ክለቦች የኦዲት ሪፖርታቸውን ካላመጡ በውድድሩ አይሳተፉም” ያሉት አቶ ኢሳያስ “ከዚህም በኋላ የኛም የፊፋም ትኩረት ብሄራዊ ቡድኖቻችን ላይ አጠንክረን የምንሰራ ይሆናል ሁሉም የዕድሜ ቡድኖችን ይመለከታል። ፋይናንስን በተመለከተ በኔጌቲፍ ጀምረን ፖዘቲቭ ላይ መገኘታችን ጥሩ ነው ነገር ግን ብዙ መስራት አለብን አንድ ስፖንሰር ሲመጣ መልካም ስም አግኝቶ እንደሚመጣ እያሰበ በመሆኑ የኢሜጅ ለውጥ ገንብተናል ይሄን እናስቀጥላለን ብለን እናምናለን” ያሉት አቶ ኢሳያስ ” እስካሁን ከሚዲያ ጋር ያለን ግንኙነት በግል ትውውቅ የሚሰራ ነው ከአሁን በኋላ ግን ከማህበሩ ጋር እየተነጋገርን በጋራ እንሰራለን የውጪ ጉዞ በግል የሚላኩ ጋዜጠኞች ጋር ተያይዞ የሚነሳው ክፍተት እንዲታረም እንጥራለን”ሲሉ ተናግረዋል።
ስለ ጠቅላላ ጉባኤው የቦታ ለውጥ የተናገሩት አቶ ኢሳያስ “ከጎንደር ወደ አዲስ አበባ ጉባኤው የተመለሰው በአካል መጥቼ ምርጫውን እበጠብጣለሁ ባለ አመራር ዛቻ ነው… ያን አመራር ደግም እንደተራ ሰው አናየውም” ያሉት አቶ ኢሳያስ “የጎንደር ከተማ በስፖርቱ በኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ለማድረግ ከ20 ቀን በላይ የፈጀ ከ20 አመት በታች ሴቶች ውድድር አድርገናል ክለቦች አንሄድም ብለው ፒቲሽን ተፈራርመው መጥተው ሳንቀበለው ቀርተን ቡድኖች ተፋልመው መጥተዋል የሁለት ቀን ስብሰባ በመለወጡ ግን የጎንደር ኢኮኖሚ ተነካ ማለት አይቻልም ጉዳዩ ለምን እንደተጋነነ አልገባኝም” ሲሉ አስረድተዋል።
አቶ ኢሳያስ “የዛሬ አራት አመት ምን ተረከብን ምን ሰራን ክፍተታችን ምንድነው የሚል ዝርዝር የያዘ 78 ገጽ የያዘ ሌጋሲ ዶክመንት አዘጋጅቻለሁ ከተመራጩ ፕሬዝዳንት ጋር አውርቼ የሰራነውን የጎደለንን ነግሬው ነው የምወጣው…. በ30 ደቂቃ አልወጣም በምርጫው ጉባኤው የወሰነው የምርጫውን ውጤት እቀበላለሁ ምክንያቱም ከግለሰብ ሀገር ይበልጣል” ሲሉ አስረድተዋል።
በካፍና በፊፋ ቦታ ለማግኘት ኢትዮጵያ መቸገሯ እንዴት ሊስተካከል ይችላል የተባሉት አቶ ኢሳያስ “እውነቱን እንነጋገር አሁን ባለው መገፋፋት መቼም ውክልና አታገኝም በካፍ ቦታ ላይ ለመገኘትና ውክልና ለማግኘት ረጅም ጊዜ መቆየት ይጠይቃል። በርግጥ አንድ ሰው ፊፋም ሆነ ካፍ ቦታ አገኘ ማለት የሀገሪቱ እግርኳስ አደገ ማለት አይደለም.. እናም ለውክልና ጊዜ የሚወስድ ይመስለኛል” ሲሉ መልሰዋል።
ለእሁዱ ምርጫ ከፊፋ ሶስት ከካፍ አንድ ተወካይ እንደሚመጡ አቶ ኢሳያስ ጅራ አስረድተዋል።