በዋንጫዉ ፉክክር ላይ ከቅዱስ ጊዮርጊስ እና ኢትዮጵያ መድን ጋር እየተፍካከረ የሚገኘዉ የአሰልጣኝ ደግአረግ ይግዛዉ ቡድን ባህርዳር ከተማ በአስራ ዘጠነኛዉ ሳምንት ሁለተኛ ቀን ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማን 3ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
ከትላንት በስቲያ ህልፈቱ ለተሰማዉ የፌደራል ረዳት ዳኛ ተስፋየ ንጉሴ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ጥሩ የሚባል የሜዳ ላይ እንቅስቃሴን ያስመለከተን ሲሆን በተለይ ባህርዳር ከተማ በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ያህል ደቂቃዎች ቶሎ ቶሎ ወደ ግብ በመድረስ በኩል የተሻሉ ሁነዉ በዚሁ ደቂቃ ላይም በመስመር ተጫዋቹ ሀብታሙ ታደሰ አማካኝነት መሪ መሆን የቻሉበት ግብ ማስቆጠር ችለዋል።
- ማሰታውቂያ -
ግብ ከተቆጠረባቸዉ በኋላ በተሻለ ማጥቃት በመጫወት የአቻነት ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት ብርቱካናማዎቹ በተቃራኒው በዕለቱ ድንቅ በነበረዉ ሀብታሙ ታደሰ ሁለተኛ ግብ ተቆጥሮባቸዉ የመጀመሪያውን አጋማሽ ሁለት ለዜሮ እየተመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በጥሩ መሻሻል የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች በ49ነኛዉ ደቂቃ ላይ በቢኒያም ጌታቸዉ አማካኝነት ወደ ጨዋታቸዉ ሊመልሳቸዉ የሚችለዉን ጎል ማስቆጠር ችለዋል። ይሄንንም ተከትሎ ቢኒያም ጌታቸዉ በውድድር አመቱ አስራ አንደኛ ጎሉን ማስቆጠር ችሏል።
በጥሩ መነሳሳት ላይ የነበሩት ድሬዎች በ64ተኛዉ ደቂቃ ላይ ግን አምበላቸዉ ብሩክ ቃልቦሬ ፉአድ ፈረጃ ላይ ጥፋት መስራቱን ተከትሎ በሁለተኛ ቢጫ በቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል።
በጎዶሎ ተጫዋች ቀሪ ደቂቃዎችን ለመቀጠል የተቸገረዉ ድሬዳዋ ከተማ በመጨረሻዎቹ ሀያ አምስት ያህል ደቂቃዎች በባህርዳር ከተማ የበላይነት ተወስዶበት የነበረ ሲሆን በ80ኛዉ ደቂቃ ላይም ሶስተኛ ግብ ተቆጥሮበታል።
በዚህም ማማዱ ሲዲቤ ከቀኝ መስመር በኩል ያሻሙን ኳስ ዱሬሳ ሹቤሳ በጭንቅላቱ በመግጨት ለራሱ ሁለተኛውን እንዲሁም ለቡድኑ ደግሞ ሶስተኛዉን ጎል ማስቆጠር ችሏል።
ዉጤቱን ተከትሎም ባህርዳር ከተማ ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በነጥብ ተስተካክሎ በግብ ክፍያ ተበልጦ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ድሬደዋ ከተማ በአንፃሩ በ24 ነጥቦች 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።