የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ (አርብ) አንድ ጨዋታ የተደረገ ሲሆን ነገ (ቅዳሜ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ሀዲያ ሆሳዕና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
የጨዋታ ቀን: ቅዳሜ ጥር 09/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ተካልኝ ለማ
የጨዋታ ቦታ: አቢዮ ኤርሳሞ ስታዲየም
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 9ኛ ሳምንት ላይ የደረሰ ሲሆን በዚህ ዙርም በውድድር አመቱ አስከፊ አጀማመር አድርጎ ከጊዜ ወደ ጊዜ የውጤት መሻሻል አሳይቶ ከወራጅ ቀጠናው መራቅ የቻለው ሀዲያ ሆሳዕና ሌላው በዘንድሮው የውድድር ዓመት ወጥ አቋም ማሳየት የተሳነው እና ከሜዳው ውጪ ማሸነፍ የተቸገረውን ቅዱስ ጊዮርጊስን በሜዳው እና በደጋፊው ፊት የሚያስተናግድ ይሆናል።
በዘንድሮው የውድድር አመት ሀድያ ሆሳዕና በሜዳው ጥሩ የሚባል ሪከርድ ሲኖረው በ3ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት አላስተናገደም። ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ከሜዳው ውጪ መጥፎ ሪከርድ ነው ማስመዝገብ የቻሉት። ምንም እንኳን በ4ጨዋታዎች አንድ ሽንፈት ብቻ ያስተናገዱ ቢሆንም በአንፃሩ 1ግብ ብቻ ነው ማስቆጠር የቻሉት። ይህንንም ተከትሎ የነገውን ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ወይም ሀድያ ሆሳዕና ያሸንፋል ብሎ በእርግጠኝነት ለመገመት አዳጋች ያደርገዋል።
- ማሰታውቂያ -
በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ከሜዳው ውጪ ሲጫወት በርካታ የግብ እድል መፍጠር አለመቻሉ እንደ ድክመት ይወሰዳል። ከዚህ በተጨማሪም ግብ የማግባት ችግር እንዳለበት የሚታወቅ ነው። ይባስ ብሎ ደግሞ በ8ኛ ሳምንት ጨዋታ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲጫወቱ የቡድኑ ወሳኝ አጥቂዎች የሆኑት ሳለሀዲን ሰዒድ እና ጌታነህ ከበደ በጉዳት መውጣታቸው ለፈረሰኞቹ ሌላ ራስ ምታት ሆኗል። ከዚህ ባሻገር ግን መሀል ሜዳ ላይ የሚጫወቱት የቅዱስ ጊዮርጊስ አይደክሜ ተጫዋቾች ሙሉዓለም መስፍን እና ሀይደር ሸረፋ ለቅዱስ ጊዮርጊስ መልካም ነገርን ያመጡለታል ተብሎ ይጠበቃል። ስለሆነም ቅዱስ ጊዮርጊስ በማሸነፍ ወደ ሊጉ መሪዎች በጣም ለመጠጋት እንዲሁም ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመሸሽ ነገ ከባድ ፍልሚያ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ቡድኑ በኢትዮጵያ ቡና 5-0 ከተሸነፈ በኋላ ያለፉትን ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ድል ማድረጉ ሜዳው ላይ ካለው ጥንካሬ ጋር ተዳምሮ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታውን ፈታኝ ሊያደርግበት ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የቢስማርክ አፖንግ ጥሩ ብቃት ላይ መገኘት ለሀድያ ሆሳዕና ጠቃሚ ነው።
በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሀድያ ሆሳዕና ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 3ቱን በሜዳው ያደረገ ሲሆን ከነዚህ 3ጨዋታዎች ሲዳማ ቡናን ሲያሸንፍ ከባህርዳር ከተማ እና ከሀዋሳ ከተማ ጋር አቻ መለያየት ችሏል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 8ጨዋታዎች 2ቱን ሲያሸንፍ 2ቱን አቻ ወጥቶ በቀሪዎቹ 4 ጨዋታዎች ሽንፈት በማስተናገድ በ8ነጥቦች ከሊጉ ግርጌ በ2ነጥቦች ከፍ ብሎ 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃሩ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች 4ጨዋታዎችን ከሜዳው ውጪ ሲያደርግ በሶስቱ ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በጅማ አባጅፋር ሽንፈት ሲያስተናግድ አንድም ጨዋታ ማሸነፍ ተስኖታል። በአጠቃላይ በሊጉ ካደረጋቸው 7ጨዋታዎች ደግሞ በ3ጨዋታዎች አሸንፎ በ4ጨዋታዎች አቻ ወጥቶ በ1ጨዋታ ብቻ በመሸነፍ የሊጉ አናት ላይ ከሚገኘው መቐለ 70 እ. በ3ነጥቦች ብቻ ዝቅ ብሎ በ13ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ነገ በሚካሄደው እና ፌደራል አርቢትር ተካልኝ ለማ በሚመሩት ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ የሚያሸንፍ ከሆነ የሊጉ መሪ መሆን የሚችል ሲሆን በአንፃሩ ባለሜዳው ሀድያ ሆሳዕና ድል የሚቀናው ከሆነ ከወራጅ ቀጠናው መራቅ ያስችለዋል።
ሀድያ ሆሳዕና በነገው ጨዋታ የመሐመድ ናስር እና የኢዩኤል ሳሙኤልን ግልጋሎት ማግኘት የማይችሉ ሲሆን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ሳለሀዲን ሰዒድ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ለዓለም ብርሀኑ ከነገው ጨዋታ ውጪ ሆነዋል። አቡበከር ሳኒ ከጉዳት በማገገሙ በነገው ጨዋታ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪም ጌታነህ ከበደ ከቡድኑ ጋር አብሮ እንደተጓዘ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።