የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በበአል ሰሞን የሚደረጉ ሲሆን ዛሬ (ማክሰኞ) አንድ እንዲሁም ነገ (ረቡዕ) ደግሞ ሰባት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። በነገው እለት ከሚደረጉት ሰባት ጨዋታዎች መካከል ሀዲያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና የሚያደርጉትን ጨዋታ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን እንደሚከተለው ዳሰነዋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ሀድያ ሆሳዕና ከሲዳማ ቡና
የጨዋታ ቀን: ረቡዕ ታህሳስ 29/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ፌደራል አርቢትር ኢብራሂም አጋዥ
የጨዋታ ቦታ: አብዮ አርሳሞ ስታዲየም
በ7ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ነገ ከቀኑ 9:00 ሲል እስካሁን በሊጉ ድል ማስመዝገብ ያልቻለው ሀዲያ ሆሳዕናን በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት ከተሳነው ሲዳማ ቡና ጋር የሚያገናኝ ይሆናል።
ሀዲያ ሆሳዕና እስካሁን በሊጉ ድል ማስመዝገብ ያልቻለ ብቸኛ ቡድን ሲሆን ነገ ይህንን መጥፎ የውድድር ጊዜ ለመቅረፍ እና 3ነጥቦች ለማግኘት ብርቱ ፉክክር ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ግን ቡድኑ በርካታ ግቦችን ከማስተናገዱ ባሻገር የግብ እድሎችን በመፍጠር እና ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ከባድ ድክመት እንዳለበት ማየት ተችሏል። ለዚህም እንደ ዋና ማሳያነት ሊጠቀስ የሚችለው ሀዲያ ሆሳዕና እስካሁን በሊጉ ያስቆጠራቸው 4ግቦች ብቻ ሲሆን በአንፃሩ 14ግቦች ተቆጥረውበታል። ከዚህም በተጨማሪ ሀድያ ሆሳዕና በሊጉ ብዙ የማስጠንቀቂያ ካርዶችን ከተመለከቱ ክለቦች ቀዳሚውን ስፍራ ሲይዙ አስራ አንድ የቢጫ ካርዶችን እና አንድ የቀይ ካርድን መመለከት ችለዋል፡፡ በተለይም በሀዲያ ሆሳዕና በኩል ደስታ ጊቻሞ ለቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች መሆኑን እያሳየበት ባለው የውድድር አመት ቡድኑ በሊጉ ካስቆጠራቸው አራት ግቦች ሁለቱን በማስቆጠር ቁልፍ ሚናን እየተጫወተ ይገኛል።
- ማሰታውቂያ -
ሲዳማ ቡና በአንፃሩ በሊጉ ወጥ አቋም ማሳየት ተስኖት በ6ኛው ሳምንት በሜዳው ሽንፈት አስተናግዶ የሊጉ አናት ላይ መቀመጥ የሚችልበትን አጋጣሚ አምክኗል። ሲዳማ ቡና በአዲስ ግደይ፣ በሀብታሙ ገዛኸኝ እና ይገዙ ቦጋለ እየተመራ ለተጋጣሚ ቡድኖች አስፈሪ መሆኑን ቢቀጥልም ውጤት አስጠብቆ የመውጣት ችግር ተስተውሎበታል።
በ6ኛው ሳምንት ጨዋታ ሀዲያ ሆሳዕና ወደ አዲስ አበባ ተጉዞ በኢትዮጵያ ቡና የ5-0 አስከፊ ሽንፈት አስተናግዶ ሲመለስ ሲዳማ ቡና በተመሳሳይ በሜዳው በድሬደዋ ከተማ የ2-1 ሽንፈት አስተናግዷል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ከሽንፈት መልስ ሙሉ 3ነጥብ ለማግኘት የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በእግር ኳስ አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። በ6ሳምንታት የሊጉ ቆይታ ሀዲያ ሆሳዕና በ2 ነጥቦች እና በ10 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኝ ሲዳማ ቡና በአንፃሩ ከመሪው ፋሲል ከተማ በ2ነጥቦች ብቻ ርቆ በ9ነጥቦች 5ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
በጨዋታው ሲዳማ ቡናዎች ብርቱ ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ ባይታሰብም ሀዲያ ሆሳዕናም በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም። ሲዳማ ቡና በጨዋታው ድል የሚቀናቸው ከሆነ የሌሎች ቡድኖች ነጥብ መጣልን ጠብቀው በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ አናት ላይ የመቀመጥ እድልን የሚያገኙ ይሆናል። ሀዲያ ሆሳዕና በአንፃሩ ባለበት የባዛ የግብ ዕዳ ምክንያት ቢያሸንፍም ከሊጉ ግርጌ ከፍ የማለት እድሉ በጣም የጠበበ ነው።
በሀዲያ ሆሳዕና በኩል በረከት ወልደዮሐንስ በጉዳት የማይገባ ሲሆን መሐመድ ናስርን ከጉዳት መልስ አግኝቷል። በሲዳማ ቡና በኩል ሚሊዮን ሰለሞን በረጅም ጉዳት ምክንያት አሁንም ወደሜዳ ያልተመለሰ ሲሆን ይህንን ቅድመ ዳሰሳ እስካጠናከርንበት ሰዓት ድረስ ሌላ የተሰማ ጉዳትም ሆነ የቅጣት ዜና አልተሰማም።