በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ14ኛ ሳምንት የቅዳሜ ብቸኛ የሊጉ ጨዋታ አ/አ ላይ ተደርጎ ኢትዮጵያ ቡናን ከ ፋሲል ከተማ ተገናኝተው ባለሜዳዎቹ ኢትዮጵያ ቡናዎች 3-2 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችለዋል።
ከጨዋታው መጀመር በፊት የኢትዮጵያ ቡናን 50ኛ ዓመት ምስረታ ምክንያት በማድረግ የፋሲል ከተማ የቡድን አመራሮች የሁለቱ ቡድኖች ፎቶ ያለበት የፎቶ ፍሬም ለኢትዮጵያ ቡና አቻዎቻቸው አበርክተዋል።
ከእስከዛሬው በተለየ እና በሁለቱም ቡድኖች እጅግ ባማረ እና በተዋበ ዝማሬና ድጋፍ የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የመጀመሪያውን ግብ ለማስተናገድ የወሰደበት የ2 ደቂቃዎች እድሜ ብቻ ነበር።
2ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ኤርሚያስ ሀይሉ ፍጥነቱን ተጠቅሞ የመጀመሪያውን ግብ በማስቆጠር ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሎ ነበር። በግቧ መቆጠር ብዙም ያልተደናገጡት ኢትዮጵያ ቡናዎች ወደ ፋሲል ከተማ የግብ ክልል ቶሎ ቶሎ ለመድረስ ጥረት አድርገዋል። በዚህም 7ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ክሪዝስቶም ንታምቢ ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። ሆኖም ግን የፋሲል ከተማ መሪነት መዝለቅ የቻለው ለ6 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። 8ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ተከላካይ ከድር ከረዲንየሰራውን ስህተት ተጠቅሞ ያገኘውን ኳስ የኢትዮጵያ ቡናው አጥቂ ሳሙኤል ሳኑሚ በጥሩ እርጋታ ወደ ግብነት ቀይሮት ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። አብዛኛው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ በመሀል ሜዳ ላይ ያተኮረ የነበረ ሲሆን ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ሊባል የሚችል እንቅስቃሴ ማድረግ ችለዋል። ሆኖም 15ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድ ናስር 2ኛ ግብ በማስቆጠር እንግዳዎቹን ፋሲል ከተማን(አፄዎቹን) በድጋሚ ቀዳሚ ማድረግ ችሏል። ከዚህች ግብ መቆጠር በኋላም አፄዎቹ ሶስተኛ ግብ በማስቆጠር ጨዋታውን ለመግደል እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ አቻ ለመሆን ተመልካቹን ቁጭ ብድግ የሚያደርግ ጨዋታ ማሳየት ችለዋል። 27ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ኤልያስ ማሞ የሞከረውን ኳስ የፋሲል ከተማው ግብ ጠባቂ ሣማኬ ሚካኤል በቀላሉ ይዞታል። ከ1ደቂቃ በኋላ 28ኛው ደቂቃ ላይ ሳምሶን ጥላሁን ከሳጥን ውጪ የመታው ኳስ በርቀት ወደ ውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ 3ደቂቃዎች በኋላ 31ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ኢያሱ ታምሩ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት ግሩም ግብ በማስቆጠር ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከግቧ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ትንሽ መቀዛቀዝ የታየ ሲሆን 33ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው ራምኬል ሎክ በሰራው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ሊሰናበት ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮጵያ ቡና በኩል የመሀል ሜዳ ክፍል ላይ ሳምሶን ጥላሁን እና ክሪዝስቶም ንታምቢ የነበራቸው ጥምረት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። በፋሲል ከተማ በኩል ዳዊት እስጢፋኖስ እና አብዱራህማን ሙባረክ በጉዳት ምክንያት ባለመኖራቸው የቡድኑን ሚዛን አዛብተውታል። በ10 ልጅ ለመጫወት የተገደዱት ፋሲል ከተማዎች በጎዶሎ ልጅ እንደመጫወታቸው ውጤቱን ለማስጠበቅ አፈግፍገው ይጫወታሉ ተብሎ ቢጠበቅም ኢትዮጵያ ቡናን ተጭነው ለመጫወት ጥረት ሲያደርጉ ተስተውለዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ግብ ጠባቂ ሀሪሰን ሄሱ ከግብ ክልሉ ውጪ ኳስ በእጁ ነክቷል በሚል የፋሲል ከተማ አሰልጣኞች እና ተጠባባቂ ወንበር ላይ የተቀመጡ ተጫዋቾች እንዲሁም ደጋፊዎች ቅሬታቸውን አቅርበዋል። ሆኖም የዕለቱ ዳኛ ጨዋታው እንዲቀጥል በማዘዝ ጨዋታው ቀጥሏል። ሆኖም ተጫዋቾቹም ሆኑ ደጋፊዎቹ ያሳዩት ያልተገባ ባህሪይ መታረም አለበት። ከዚህ አጋጣሚ በኋላ የፋሲል ከተማ ክለብ የክስ ሪዘርቭ ማስያዝ ችሏል።
በጨዋታው 40ኛ ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው ተከላካይ አስራት ቶንጆ ከቀኝ በኩል ያሻገረለትን ኳስ አጥቂው ሳሙኤል ሳኑሚ በግንባሩ ገጭቶት ወደውጭ ወጥቷል። ከዚህ ሙከራ በኋላም ይሄ ነው የሚባል ሙከራ ሳይደረግ የመጀመሪያው 45 ደቂቃ ተጠናቆ ሁለቱ ቡድኖች ወደ መልበሻ ቤት አምርተዋል።
በሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አጋማሽ በተቃራኒ በሁለቱም ቡድኖች በኩል እጅግ የተቀዛቀዘ ጨዋታ መመልከት ችለናል። ኢትዮጵያ ቡና ያገኘውን የአንድ ተጫዋች ብልጫ በአግባቡ በመጠቀም በመሀል ሜዳ ላይ ብልጫ መውሰድ ችሏል። ሆኖም ግን ይሄንን ብልጫ ወደ ግብነት በመቀየሩም ሆነ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ረገድ ደካማ ሆኖ ተስተውሏል። ሆኖም ግን 60ኛው ደቂቃ ላይ ክሪዝስቶም ንታምቢን ቀይሮ የገባው የኢትዮጵያ ቡናው አቡበከር ናስር ግብ በማስቆጠር ኢትዮጵያ ቡናን መሪ ማድረግ ችሏል። ከዚህ ግብ መቆጠር በኋላ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ወደ ግብ ለመድረስ የተደረገው ጥረት እጅግ ደካማ ነበር። 74ኛው ደቂቃ ላይ የፋሲል ከተማው መሀመድ ናስር የመታው ኳስ ወደ ውጭ ወጥቷል። ጨዋታው ሊጠናቀቅ 7ደቂቃዎች ሲቀሩት 83ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናው አስናቀ ሞገስ ከግራ በኩል ያሻገረለትን ኳስ አቡበከር ናስር በግሩም ሁኔታ በግንባሩ ገጭቶት ግብ ጠባቂው ይዞታል። ከዚህች ሙከራ በኋላ የረባ እንቅስቃሴ ሳይታይበት ጨዋታው በኢትዮጵያ ቡና 3-2 አሸናፊነት ተጠናቋል።
የአሰልጣኞች አስተያየት
ም/አሰልጣኝ መሀመድ ኢብራሂም(ኪንግ)—- ኢትዮጵያ ቡና
“የዛሬው ጨዋታ እንደ ተመለከታችሁት ትንሽ ጫና የነበረበት ጨዋታ ነበር፤ ሜዳችን ላይ ያስመዘገብነው ነጥብ ለወደፊት የሚያነቃቃ እና የሚያበረታታ ነው፤ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ፋሲል እኛ ላይ ጫና ፈጥሮ መጫወት ችሎ ነበር፤ እራሳችንን አሻሽለን ማሸነፍ ችለናል።”
አሰልጣኝ ምንተስኖት ጌጡ—- ፋሲል ከተማ
“ኢትዮጵያ ቡና በኳስ ቁጥጥሩ ጥሩ ነበር፤ እኛም ራምኬል ሎክ በቀይ እስከሚወጣ ያደረግነው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር፤ እንደ እንቅስቃሴው ውጤቱ ለኛ ይገባን ነበር። ነገር ግን ያልተገቡ የዳኝነት ውሳኔዎች የኛን ቡድን እንዲወርድ አድርገውታል። ለእነሱ(ኢትዮጵያ ቡና) የሚደረጉ ውሳኔዎች እና ለኛ የሚደረጉ ውሳኔዎች ሚዛናዊ አልነበሩም፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ቡና ሳይሆን ዳኛ አሸነፈን ነው ማለት የምችለው።”