ስመ ጥሩ ጋዜጠኛ ባደረበት ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ ማክሰኞ ጥር 14/2016 ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱ ተሰምቷል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) በአሻም ቴሌቪዥን “የገነነ” እና “ጥቁር እንግዳ” የተሰኙ ፕሮግራሞችን አዘጋጅ እና አቅራቢ ሆኖ እንዳገለገለ ጣቢያው ገልጧል። ጋዜጠኛ ገነነ መኩሪያ ለበርካታ ዓመታት ለተለያዩ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተወዳጅ የሆኑ ዝግጅቶችን በማቅረብ ሠርቷል።
ገነነ መኩሪያ እግር ኳስ እና ፖለቲካን እንዲሁም ታሪክን የሚዳስሱ በርካታ መጽሐፎችን ያሳተመ ሲሆን፣ “ኢሕአፓ እና ስፖርት” እና ሌሎች መፃሕፍትን ለአንባቢ አቅርቧል።
ሊብሮ ከስፖርት ጋዜጠኝነት ሕይወት ባሻገር በወጣትነት ዘመኑ ለበርካታ የእግር ኳስ ክለቦች በመሠለፍ ተጫውቷል።
ገነነ ከ30 ዓመታት በላይ በስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያው አስተዋጽኦ ያበረከተ ሲሆን በጋዜጣ፣ በሬዲዮ እና በቴሌቪዥን እንዲሁም በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሥራውን በማቅረብ ተወዳጅነትን አትርፏል።
ገነነ መኩሪያ በዘመናት የዳበረ የስፖርት፣ የፖለቲካ፣ የሙዚቃ እና የማኅበራዊ ጉዳይ ታሪኮችን በጥልቀት እና በዝርዝር የሚያውቅ ሲሆን፣ በስፖርት እና በፖለቲካ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ መጽሐፍትን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል።
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዳለው ገነነ መኩሪያ ለእግር ኳስ ስፖርት ላበረከተው ታላቅ አስተዋፅኦም በአዲስ አበባ ተሰናድቶ በነበረው የካፍ ኮንግረስ ላይ የረጅም ዘመን አግልግሎት ሜዳሊያ ተበርክቶለታል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ጋዜጠኞች ማህበር ( ኢስጋማ) ለመላው ቤተሠቦቹ እና የስራ ባልደረቦቹ መፅናናትን ይመኛል።