የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ራሳቸውን ከክለቡ ሃላፊነት ማንሳታቸውን አስታወቁ።
አመራሮቹ ተፈጠሩ ያሏቸውን ሰባት ዝርዝር ምክንያቶችን በመዘርዘር ችግሩን ለማስወገድ የሚችሉትን ቢጥሩም ምላሽ ባለማግኘታቸው ስራቸውን እንዳቆሙ ለወልቂጤ
ከተማ አስተዳደርና ለጉራጌ ዞን አስተዳደር ባስገቡት ደብዳቤ አሳውቀዋል።
በአመራሮቹ እንደ ምክንያት ያቀረቡት አሁን ያለው የፖለቲካ አመራር ክለቡን የጋራ አለማድረጉ፤ክለቡን ከድጎማ ነጻ ለማድረግ ያስችላሉ የተባሉ ዋና ዋና ጉዳዮችን ወደ አምራች ድርጅቶችና ህዝቡ ለማውረድ ለማስተባበርና ከፊት በመሆን በመሪነት ለመጓዝ ፍቃደኛ አለመሆን፤ በየአመቱ የሚበጀትለት በጀት አናሳ መሆኑ በጀቱም ዕቅዱን ያላገናዘበ በተጨማሪም ያለው በጀት በጊዜው የማይሰጥ መሆኑ እንደምክንያት ካስቀመጧቸው መሃል ይጠቀሳሉ።
አመራሮቹ እንዳስረዱት ጠቅላላ ጉባኤ ለማካሄድ የጎደሉ አመራሮችን ለመተካት ብንጠይቅም ምላሽ አለማግኘት የፖለቲካ ፍላጎት መኖሩና ስፖርትን በማጠቃለል በተጠመዱ አመራሮች አለመሳካቱ፤ ከፍተኛ የበጀት ዕጥረት መከሰቱና እስከግለሰብ ዕዳ ድረስ መድረሱ ይህም በተለያየ ቦታ ገጽታ ያበላሽ መሆኑ፣ የከተማና የዞን ሴክተር ውስጥ የሚገኙ በባለሙያና በአመራርነት የሚሰሩ ደግሞ ክለቡን ለማፍረስ በድብቅ የተደራጁ መንግስታዊ መዋቅር ውስጥ መኖራቸው ለውሳኔ ካበቃቸው ምክንያት መሃል ተጠቅሰዋል።
- ማሰታውቂያ -
አመራሮቹ በያዙት ጠንካራ አቋም እንዳረጋገጡት ከላይ የተጠቀሱት ምክንያቶች የክለቡን ህልውና መፈታተኑና ከስራ አስፈጻሚ አቅም በላይ በመሆናቸው ከዛሬ ጀምሮ ከሃላፊነት መልቀቃቸው አሳውቀዋል።