በካናዳ ቶሮንቶ ለ22ኛ ግዜ በተካሄደው የቲ.ሲ.ኤስ ቶሮንቶ ዋተር ፍሮንት ማራቶን ኢትዮጵያዊቷ ቡዜ ድሪባ የሴቶቹ ውድድር አሸናፊ ስትሆን አዱኛ ታከለ በወንዶቹ ፉክክር ሁለተኛ ወጥቷል፡፡
በጣም የተቀራረበ ፉክክር የታየበት የሴቶቹ ውድድር ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉትን ደረጃዎች ይዘው ያጠናቀቁበት ሆኗል፡፡ የሴቶቹ አሸናፊ የተለየችው በመጨረሻዎቹ ጥቂት ሜትሮች በተደረገ የፈጣን አጨራረስ ፉክክር ነበር፡፡ ከአስረኛው ኪሎ ሜትር ጀምሮ ተሳታፊ የነበሩት ስድስቱም ኢትዮጵያውያን አትሌቶች (ቡዜ ድሪባ፣ ዋጋነሽ መካሻ፣ አፈራ ጎድፋይ፣ ፎዚያ ጀማል፣ መሰረት ገብሬ፣ እና ቦንቱ በቀለ) በመሪነት የውድድሩን አጋማሽ 01፡11፡01 በሆነ ሰዓት ያለፉት ሲሆን ይጓዙበት የነበረው ፍጥነትም የቦታውን ሪኮርድ ለማሻሻል የሚያስችል ነበረ፡፡ ከሰላሳ አምስተኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ለአሸናፊነት የሚደረገው ፉክክር በአራቱ ኢትዮጵያውያን ቡዜ ድሪባ፣ ዋጋነሽ መካሻ፣ አፈራ ጎድፋይ፣ እና ፎዚያ ጀማል መካከል ነበር፡፡ አራቱ አትሌቶች በፊት መሪነቱ ስፍራ እየተፈራረቁ እስከመጨረሻው እግር በእግር ተከታትለው ከሄዱ በኋላ ፈጣን የአጨራረስ ብቃቷን የተጠቀመችው ቡዜ ድሪባ 2፡23፡11 በሆነ የራሷ ምርጥ ሰዓት አንደኛ ወጥታለች፡፡ ከቡዜ ጋር የመጨረሻውን ፉክክር ያደረገችው የዘንድሮ የኦታዋ ማራቶን አሸናፊዋ ዋጋነሽ መካሻ በ2፡23፡12 የሁለተኛነቱን ደረጃ ይዛ ስታጠናቅቅ አፈራ ጎድፋይ በ2፡23፡15 ሶስተኛ ወጥታለች፡፡ ፎዚያ ጀማል (2፡23፡18)፣ መሰረት ገብሬ (2፡29፡54)፣ እና ቦንቱ በቀለ (2፡31፡33) በቅደም ተከተል አራተኛ፣ ሰባተኛ እና ዘጠነኛ ሆነው ጨርሰዋል፡፡ ቡዜ ሶስተኛ የማራቶን ውድድሯን ባደረገችበት የቶሮንቶ ውድድር ላይ በማራቶን የመጀመሪያ የአሸናፊነት ውጤት ከማስመዝገቧ በተጨማሪም የራሷን ምርጥ ሰዓት በ4 ደቂቃ ከ55 ሰከንድ አሻሽላለች፡፡
ከስድስት ዓመት በላይ መቀመጫዋን በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ኒው ሜክሲኮ አድርጋ የቆየችው ቡዜ ከአንድ ዓመት በፊት ወደኢትዮጵያ በመመለስ በአሰልጣኝ ገመዱ ደደፎ ስር ስትሰለጥን ቆይታለች፡፡ ለዘንድሮው የቶሮንቶ ማራቶን ዝግጅት ከመጀመሯ በፊት ባለፈው ግንቦት ወር በፔንሲልቬንያ የተካሄደው ፒትስበርግ ግማሽ ማራቶን አሸናፊ ስትሆን በነሐሴ ወር በማሳቹሴትስ ፋልመዝ በተካሄደ የሰባት ማይል የጎዳና ላይ ሩጫ ተሳትፎዋ ስድስተኛ ወጥታለች፡፡ የማራቶን የዓለም ሻምፒዮኗ አማኔ በሪሶ እና የርቀቱ የዓለም ሪኮርድ ባለቤት ትግስት አሰፋ በሚሰለጥኑበት ስብስብ ውስጥ የተዘጋጀችው ቡዜ ከቶሮንቶ ድሏ በኋላ በሰጠችን አስተያየት ‹‹ትንሽ ነፋስ እና ቅዝቃዜ የነበረ ቢሆንም ከዚህ ቀደምም በመሰል ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ውስጥ የመወዳደር ተሞክሮ ስለነበረኝ ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ ወደ ውድድሩ የመጣሁት የራሴን ምርጥ ሰዓት አሻሽላለሁ ብዬ ነበረ፡፡ አራት ሆነን ወደውድድሩ መጨረሻ ስንቃረብ ከተፎካካሪዎቼ ትንሽ የተሻለ የአጨራረስ ብቃት እንዳለኝ ስላሰብኩ እንደማሸንፍ ተሰምቶኛል›› ብላለች፡፡
በውድድሩ ላይ ሶስተኛ ሆና ያጠናቀቀችው አፈራ ጎድፋይም ውድድሩን ለማሸነፍ አቅዳ መምጣቷን ጠቅሳ ‹‹አራት ሆነን ተያይዘን ወደመጨረሻው በተቃረብን ግዜ የተሻለ የአጨራረስ ብቃት ያላት ቡዜ ልታሸንፍ እንደምትችል አምኛለሁ እናም የሁለተኛነቱን ደረጃ ለማግኘት የምትችለውን ያህል ሞክሬያለሁ፡፡ ሆኖም ያም ሳይሳካ ሶስተኛ ሆኜ ልጨርስ በቅቻለሁ›› ብላለች፡፡
- ማሰታውቂያ -
በወንዶቹ ፉክክር ባለፈው ሚያዝያ ወር ቪዬና ላይ ባደረገው የመጀመሪያ የማራቶን ተሳትፎው ሰባተኛ ሆኖ ያጠናቀቀው ኬንያዊው ኤልቪስ ኪፕቾጌ ቼቦይ በርቀቱ የመጀመሪያ ድሉን ቶሮንቶ ላይ ለማስመዝገብ በቅቷል፡፡ ኬንያዊው ያሸነፈበት 2፡09፡20 የሆነ ሰዓትም የራሱን ምርጥ ሰዓት በአንድ ደቂቃ ከአንድ ሰከንድ ያሻሻለበት ሆኗል፡፡ ኢትዮጵያዊው አዱኛ ታከለ በ2፡10፡26 ሁለተኛ ሆኖ ሲጨርስ በርቀቱ የመጀመሪያ ውድድሩን ያደረገው ኬንያዊው አልፍሬድ ሙክቼ ኪፕቺርቺር በ2፡10፡56 ሶስተኛ ወጥቷል፡፡ ኢትዮጵያዊው ዮሀንስ መካሻ በ2:13:47 አራተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ ኢትዮጵያውያኑ መንግስቱ ዘላለም ከ21 ኪሎ ሜትር በኋላ እና አብደላ ጎዳና ከ30ኛው ኪሎ ሜትር በኋላ ውድድሩን አቋርጠዋል።
በወንዶቹ ውድድር ላይ በሁለተኛነት የጨረሰው ኢትዮጵያዊው አዱኛ ታከለ ከውድድሩ በኋላ በሰጠው አስተያየት ‹‹አሯሯጮቹ መጀመሪያ ላይ ትንሽ ከማፍጠናቸው ውጪ ውድድሩ ጥሩ ነበር፡፡ ንፋስ በነበረበት የመወዳደሪያ ስፍራ በኪሎ ሜትር ሁለት ደቂቃ ከሀምሳ ሰባት ሰከንድ እየሄዱ የነበረ መሆኑ ጥሩ አይደለም፡፡ እንደዛም ሆኖ ሁለተኛ መውጣት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ፡፡ የማሸነፍ ግብን ይዤ ብመጣም ንፋሱ እና የአሯሯጮቹ ፍጥነት ያሰብኩትን እንዳላሳካ ትንሽ ተፅዕኖ ፈጥሮብኛል፡፡ ለዚህ ውድድር ጥሩ ስዘጋጅ የነበረ ቢሆንም በመሐል የአኪለስ ሕመም ያስቸግረኝ ነበረ፡፡ በዚህም ምክንያት የፍጥነት ልምምድ እንደፈለግኩ አልሰራም ነበረ፡፡ የፍጥነት ልምምዱን እንደፈለግኩ ብሰራ ኖሮ ልጆቹ በፍጥነት ሲሄዱ አብሬያቸው መሄድ እችል ነበረ፡፡ ግን በደንብ ስላልሰራሁ ያንን መቋቋም አልቻልኩም›› ብሏል፡፡
በውድድሩ ላይ በወንዶች ከ2:07:00 በታች በሆነ ሰዓት ለሚጨርስ አሸናፊ እና በሴቶች ከ2:22:30 በታች በሆነ ሰዓት ለምትጨርስ አሸናፊ ይሰጣል ተብሎ የነበረውን 5,000 የካናዳ ዶላር የሰዓት ጉርሻ በሁለቱም ፆታዎች ያሳካ አልተገኘም፡፡
በሁለቱም ፆታዎች ውድድሩን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ባሉት ደረጃዎች ውስጥ ሆነው ያጠናቅቁ አትሌቶች በደረጃ ቅደም ተከተላቸው መሰረት ተከታዩን የገንዘብ ሽልማት በካናዳ ዶላር የሚያገኙ ይሆናል፡፡
1 ኛ – 20,000 ዶላር
2 ኛ – 10,000 ዶላር
3 ኛ – 7,000 ዶላር
4ኛ – 4,000 ዶላር
5ኛ – 3,000 ዶላር
6 ኛ – 2,000 ዶላር
7ኛ – 1,500 ዶላር
8 ኛ – 1,000 ዶላር
©️ BIZUAYEHU TESFU WAGAW