ላለፉት ስድስት አመታት በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በጨዋታ ተንታኝነት ፣ በአስተርጓሚነት እና በምክትል አሰልጣኝነት ያገለገለዉ አዲስ ወርቁ ወደ ሌላ ሀላፊነት ለማምራት በመወሰኑ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያለዉን ሀላፊነት መልቀቁን በዛሬው እለት አስታዉቋል።
አዲስ ወርቁ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ያለዉን ሀላፊነት ከለቀቀ በኋላ የሚከተለዉን መልዕክት አስተላልፏል
“ባለፉት ሁለት ዓመታት በርካታ የውጪ ሀገር የስራ እድሎችን ማግኘት ብችልም የግል እድገቴን እና ጥቅሜን ወደ ጎን በመተው ቅድሚያውን ለክለቤ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሰጥቻለሁ። ክለቡ በእጅጉ ሲፈልገኝ የኡጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ስራዬን በመሀል አቋርጫለሁ። ከዚህም ውጪ ከተለያዩ ሀገራት የሥራ ውል ቢቀርብልኝም ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆንኩም። ለዚህም ምክንያቴ አንድ እና አንድ ብቻ ነበር። በቅዱስ ጊዮርጊስ መጨረስ የነበረብኝ ሥራ ነበር። የእኔን ሙያዊ እገዛ የሚፈልግ ኃላፊነት ነበረብኝ።
- ማሰታውቂያ -
በአሁን ሰአት ግን የተግባር እውቀቴን ይበልጥ ማሳደግ የሚገባኝ ወቅት ላይ ተገኝቼያለሁ። ራሴን ለአዲስ ፈተና እና ለአዲስ የስራ ልምድ ማዘጋጀት ተገቢ ነው ብዬም አምኜያለሁ። ከእነዚህ መነሻነት ከኢትዮጵያ ውጪ ለመስራት ወስኛለሁ። ከቀረቡልኝ የሥራ ውሎች ውስጥ አንደኛውን ተቀብያለሁ።”