የአዳማ ቆይታ የመጨረሻ በሆነዉ የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ22ተኛ ሳምንት መርሐግብር ሶስተኛ ቀን ጨዋታ የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኙ ቡድን መቻል ድሬዳዋ ከተማን 2ለ1 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በአንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ተበላልጠዉ አስረኛ እና አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ሁነዉ የዕለቱን የቀን ዘጠኝ ሰዓት ጨዋታቸዉን ለማከናወን እና በጥሩ ደረጃ ላይ ተቀምጠዉ ደግሞ ቀጣዩ የሊጉ መርሐግብር ወደሚደረግባት ሀዋሳ ከተማ ለማቅናት ወደ ሜዳ በገቡት የሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያዎቹ አስር ያህል ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ያሰቡትን የጨዋታ መንገድ በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለመተግበር ሲጥሩ ተመልክተናል።
በተለይ የተጋጣሚ ቡድን በነፃነት ኳሶችን ተቀባብሎ አደጋ እንዳይፈጥርባቸዉ ክፍተቶችን በመዝጋት በሚገኙ አጋጣሚዎች በቶሎ ወደ ድሬዳዋ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ የነበሩት መቻሎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ13ተኛው ደቂቃ ላይ መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ ማስቆጠር ችለዋል። በዚህም ከቀኝ የመቻል የማጥቃት መስመር በኩል ከበሀይሉ የተቀበለዉን ኳስ አማካዩ ከንዓን በግሩም አጨራረስ ወደ ግብነት በመቀየር ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
- ማሰታውቂያ -
በዚህ ሂደት በቀጠለዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታም ከግቡ መቆጠር ከአስር ደቂቃዎች በኋላ መቻል ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ ነበር ፤ በዚህም በዕለቱ ድንቅ ሲንቀሳቀስ የነበረዉ ከንዓን ማርክነህ ለሳሙኤል ሳሊሶ ጥሩ ኳስ አቀብሎት ተጫዋቹ ኳሷን ሳይጠቀምባት የቀረባት አጋጣሚ በመቻል በኩል የተደረገች ተጠቃሽ ሙከራ ነበረች።
የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በመጣ ቁጥር ጫናቸዉን አጠንክረዉ የቀጠሉት መቻሎች በ25ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አስቆጥረዋል። በዚህም ለመጀመሪያው ግብ መቆጠር ቁልፍ ሚና የነበረዉ በሀይሉ ሀለይለማርያም ያቀበለውን ኳስ አጥቂዉ እስራኤል እሸቱ ወደ ግብነት በመቀየር የክለቡን መሪነት ወደ ሁለት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸዉን ግብ ለማግኘት እና በጨዋታውም ተጠቃሽ ሙከራ ለማድረግ የተቸገሩ የሚመስሉት ድሬዳዋ ከተማዎች በመጀመሪያ አጋማሽ ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን ተሻሽለዉ የተመለሱት ድሬዳዋ ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይ የነበሩ ቢመስሉም ነገር አሁንም ግልፅ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲቸገሩ ተስተውሏል። ያላቸዉን የሁለት ለዜሮ መሪነት አስጠብቀዉ ለመዉጣት ያለሙ የሚመስሉት መቻሎች በተቃራኒው አልፎ አልፍ ጥሩ የሚባሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችለዉ የነበረ ቢሆንም ቸጨማሪ ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዉ በተቃራኒው ግብ አስተናግደዋል።
በዚህም በርከት ያሉ ተጫዋቾችን ቀይረዉ ወደ ሜዳ ያስገቡት ድሬዳዋ ከተማዎች በተለይ በ88ተኛዉ ደቂቃ ላይ ከመዓዘን ምት የተገኘዉን ኳስ ጋዲሳ መብራቴ ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ ውብሸት እንደምንም ኳሷን ተቆጣጥሯታል ፤ መደበኛዉ ዘጠና ደቂቃ ተገባዶ በጭማሪ ሰዓት ግን ድሬዎች በሙህዲን ሙሳ አማካኝነት ግብ አስቆጥረዉ የነበረ ቢሆንም ጨዋታዉ ግን በመቻል 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ዉጤቱን ተከትሎ መቻል ነጥቡን 29 በማድረስ አስረኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ፤ በተቃራኒው ሽንፈት ያስተናገደዉ ድሬዳዋ ደግሞ በ27 ነጥቦች አስራ አንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።