በ15ተኛዉ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሐግብር የመጀመሪያ ዕለት ጨዋታ ቀን ዘጠኝ ሰዓት ላይ ባለ ሜዳዉ ክለብ አዳማ ከተማ እና ኢትዮጵያ መድን መርሐግብራቸዉን አድርገዉ ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት አገባደዋል ።
በአዳማ ከተማዎች የበላይነት በጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ የመጀመሪያ ደቂቃ ላይ ገና በመባቻዉ በአምስተኛዉ ደቂቃ አዳማ ከተማዎች ግብ ማስቆጠር ችለዋል ፤ በዚህም መነሻዋን ከማዕዘን ምት ያደረገችዉን ኳስ ዮሴፍ ታረቀኝ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ሲሆን ኳሱ ሲመልስም ሌላኛዉ የፊት መስመር ተጫዋች ቢኒያም አይተን ኳሷን ወደ ግብነት ቀይሮ አዳማዎች መሪ መሆን ችለዋል ።
ተደጋጋሚ ሙከራዎች ሲጋፈጡ የቆዩት መድኖች ከመጨዋታዉ አጋማሽ በፊት የፊት መስመር ተጫዋቹ ወገኔ ገዛኸኝ ድንቅ ሙከራ ማድረግ ችሎ የነበረ ቢሆንም በግብ ጠባቂዉ ሰይድ ሀብታሙ ድንቅ ብቃት ከሽፍበታል።
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ የማጥቃት ሃይላቸውን አጠናክረዉ የቀጠሉት እና ድንቅ ድንቅ የሚባሉ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ የቀጠሉት አዳማዎች ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ68ተኛዉ ደቂቃ ላይ ተጨማሪ ግብ አክለዋል ። በዚህም ከኋላ መስመር የተጣለውን ኳስ የኢትዮጵያ መድኑ ተከላካይ ያሬድ ካሳ በሚገባ ማፅዳት ባለመቻሉ ምክንያት የተገኘዉን ኳስ አጠገቡ የነበረዉ ቢኒያም አይተን ለራሱ እንዲሁም ለቡድኑ ሁለተኛ ጎሉን ከመረብ አሳርፏል።
ሁለተኛዉን ግብ ካስተናገዱ በኋላ ምላሽ ለመስጠት በተደጋጋሚ ጫና ፈጥረዉ መጫወት የጀመሩት መድኖች ዉጥናቸዉ ሰምሮ በ70ኛዉ ደቂቃ ግብ አስቆጥረዋል ፤ በዚህም ንጋቱ ከርቅት በቀጥታ ወደ ግብ የላከዉን ኳስ የግብ ዘቡ ሰይድ ሲመልሰዉ ጥሩ አቋቋም ላይ ይገኝ ነበረዉ ብሩክ ወደ ግብነት መቀየር ችሏል። ከዚች ግብ መቆጠር ከ12 ደቂቃዎች በኋላም ወገኔ ገዛኸኝ ከመስመር በኩል ያሻገራትን ኳስ ያሬድ ዳርዛ ወደ ግብነት ቀይሮ ተጠባቂዉ መርሐግብር ሁለት አቻ በሆነ ዉጤት ተጠናቋል።
በሌላኛዉ የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቡናማዎቹ ከተከታታይ ሶስት ጨዋታዎች በኋላ አቻ ተለያይተዋል !!
አመሻሽ 12 ሲል በተጀመረዉ የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ቡናማዎቹ ከራሳቸዉ የግብ ክልል ጀምረዉ በቅብብል በመዉጣት ወደ ተቃራኒ የሜዳ ክፍል ለመድረስ ሲጥሩ ፤ በተቃራኒው ሀምበሪቾዎች አብዝሀኛዉን ጊዜ ወደ ራሳቸዉ የግብ ክልል አፈግፍገዉ በመጫወት አልፎ አልፎ በሚገኙ አጋጣሚዎች አደጋ ለመፍጠር ሲጥሩ የተስተዋለ ቢሆንም በሁለቱም ክለቦች በኩል ይህ ነዉ የሚባል ተጠቃሽ ኢላማዉን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ለዕረፍት ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ደካማ የሚባል እና ሙከራ አልባ የነበረ የመጀመሪያ አጋማሽ ያሳለፉት ሁለቱ ክለቦች በሁለተኛዉ አጋማሽ በተሻለ መነቃቃት ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተስተዉሏል ፤ በዚህም ከነበሩት ሙከራዎች መካከል በ51ኛዉ ደቂቃ ላይ ቡናማዎቹ በአንተነህ ተፈራ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለዉ የነበረ ቢሆንም ኳሱ ወደ ዉጭ ወጥቷል ። ከተጠበቀዉ በተቃራኒው በሙከራ እረገድ የተቀዛቀዘ በነበረዉ ሁለተኛዉ አጋማሽ ቡናማዎቹ ይበልጥኑ ወደ ፊት ተጠግተዉ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደርጉት የነበረዉ ጥረት ሳይሳካ በአንፃሩ በራሳቸዉ የግብ ክልል ጥቅጥቅ ብለዉ ይከላከሉ የነበሩት ሀበሪቾዎች ግን ዉጥናቸዉ ሰምሮ ግብ ሳይቆጠርባቸዉ ጨዋታ 0ለ0 በሆነ አቻ ዉጤት ተገባዷል።