የ2015 ዓ.ም የኢትዮጵያ ወንዶች ከፍተኛ ሊግ እና አንደኛ ሊግ የውድድር መጀመርያ ቀን እና የዕጣ ማውጣት መርሐ ግብር የሚከናወንበት ዕለት ተገለፀ።

የ2015 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ከፍተኛ እና አንደኛ ሊጎች የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ከጳጉሜ 1 ጀምሮ ክፍት መደረጉ የሚታወስ ሲሆን ከተሳታፊዎች ብዛት አንፃር ውድድሮችን በጊዜ ለመጀመር በማሰብ የውድድር ዳይሬክቶሬት የውድድሮቹ መጀመርያ እና የዕጣ ማውጣት ቀንን አሳውቋል።

በዚህም መሠረት የከፍተኛ ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርዓት ጥቅምት 28 የሚደረግ ሲሆን የአንደኛ ሊግ ደግሞ ጥቅምት 29 ይከናወናል። ህዳር 3 ደግሞ ሁለቱም ውድድሮች የሚጀመሩበት ቀን እንዲሆን ተወስኗል። በተጨማሪም እስከ ህዳር 15 የነበረው የሁለቱ ሊጎች የተጫዋቾች የዝውውር ጊዜ የቀን ሽግሽግ ተደርጎበት እስከ ጥቅምት 25 ብቻ እንደሚከናወን ተገልጿል።