“የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በፖለቲካዊ ጫናና ማስፈራሪያ የተወሰነ ነው”
“በገንዘብ ያልተታለሉና ፖለቲካዊ ማስፈራሪያውን ያልፈሩ 27 መራጮቼ መመስገን አለባቸው”
አቶ መላኩ ፈንታ
/ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ተወዳዳሪ”
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ምርጫ በውድድር መሆኑ ቀርቶ በገንዘብና የፖለቲካ ውሳኔ የተሰጠበት ሆኗል” ሲሉ አቶ መላኩ ፈንታ ተናገሩ።
- ማሰታውቂያ -
ከአማራ ክልል እግርኳስ ፌዴሬሽን የተወከሉትና በምርጫው በ27 ነጥብ ሁለተኛ ሆነው የፈጸሙት አቶ መላኩ ዛሬ በሰጡት መግለጫ “በገንዘብም ይሁን በፖለቲካ ተጽዕኖ ምርጫውን ማድረግ ለጊዜው ቢጠቅምም አዋጪ አይደለም አክሳሪ ነው” ሲሉ አስረድተዋል። አቶ መላኩ”ምርጫው ምክንያታዊ በሆነ ሂደት የሚደረግ ምርጫ እንዲሆን ሌላው መንገድ እንደማይጠቅም ገልጸናል አስፈላጊ በሆነ ህጋዊ መንገድ አላማችንን የመግለጽ ስራ ሰርተናል ” ሲሉ የሄዱበትን ሂደት አስረድተዋል።
አቶ መላኩ እንደገለጹት ” የምርጫው ሂደት ከፍ እንዲልና ለሌላው አስተማሪ እንዲሆን ለማድረግ ሰርተናል በዚህ አጋጣሚ ህዝብና ሚዲያው ባቀረብነው የምርጫ ዘመቻ እንድንመረጥ ድጋፍ አድርጎልናል ብስራትና ቲክቫም የህዝብ መጠየቅና አስተያየት በማቅረብ ህዝብ በምክንያት እንደሚመርጥ አይተንበታል ሚዲያውና ህዝቡ ዳኝነት እንደሚሰጥም ተረድተናል” ሲሉ ተናግረዋል።
“ያለፈው ምርጫ ዕጸጾችን በድፍረት ገልጸን መታረም እንዳለበት ብንገልጽም ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ ግን ጨዋታው ተቀየረ ያሉት አቶ መላኩ” ከረቡዕ ጀምሮ መልኩ ተቀየረ መቀየሩንም እናውቃለን ውጤቱንም እናውቃለን ነገር ግን እንቀጥላለን ብለን ነው የሄድንበት..ምርጫው ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውሳኔ የተሰጠበት ነው”ሲሉ ተናግረዋል።
አቶ መላኩ እንደገለጹት ” የምርጫው አካሄድ ተቀይሯል ተለውጧል ብለን እናምናለን በተለይ ከዓርብ ደምሮ ደግሞ አይን ባወጣ መልኩ በግልጽ በ24 ሰዓት ውስጥ ውጤቱ እንደሚገለበጥ ተነግሮናል መረጃውም ደርሶናል ማርሽ ቀያሪ ወይም ውጤት ቀያሪ የተባሉ ፖለቲካዊ ውሳኔዎች ስለተላለፉ ለውጦቹ ሊታዩ ችለዋል” ሲሉም ይናገራሉ።
” ከዓርብ ጀምሮ የአዲስ አበባ ምሽቶች ትልልቅ ሆቴሎች የአንዳንድ ትልልቅ ሰዎች መኖሪያ ቤቶች ባህሪያቸውን ቀይረው የድርድር ቦታዎች ሆነዋል ትላልቅ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች መገናኛዎችና ክፍያ ማስፈጸሚያዎች ሆነዋል የቢሮ ስልኮች ደግሞ ፖለቲካዊ ትዕዛዞች የሚሰጥባቸው ለመራጮች ፖለቲካዊ ማብራሪያና ማሳሰቢያ የተሰጡበት ሆነዋል” ሲሉ አስረድተዋል።
“ጉባኤያቸውን እስከ ምሳ ሰዓት ድረስ ቁጭ ብዬ ተከታትያለሁ ያም ለሀገሬም ሆነ ለእግርኳሳችን ክብር ስላለኝ ነው በጉባኤው የተገኘሁት ጉባኤውን ከማክበር እንጂ ውጤት እናመጣለን ብዬ አይደለም ውጤት ለማድመቅ መገኘት እንደሌለብኝ አውቃለሁ መረጃዎቹ ለነገ ለውጥ የሚያመጡ ከሆነ የሚጠቀምባቸው ካለ ለማስተካከል እንዲረዳ መግለጼ ነው” ያሉት አቶ መላኩ ” መራጮች የተመረጡት ፕሬዝዳንትና ስራ አስፈጻሚዎችን ካልመረጡ ምን እንደሚደርስባቸው ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው መምጣታቸው የሚታወቅ ነው ከዚህ ውጪ ከፍተኛ የገንዘብ ቅብብልም ነበር የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች የሆኑት ግን ደፍረው የገንዘብ ቅብብሉን እጅ ከፍንጅ አስይዘው በፖለቲካዊና በባለስልጣናት ትዕዛዝ እንዲለቀቁ ተደርጓል በምርጫው ሂደት አሳዛኝ ድርጊት ተከስቷል ማን ፕሬዝዳንት ማን ስራ አስፈጻሚ እንደሚሆን አስቀድመን አውቀናል ይሄ ከገንዘብና ከፖለቲካዊ ትዕዛዝ ያገኘናቸው መረጃዎች ናቸው” ሲሉም አስረድተዋል።
ስለ የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሃይሉ ሞላ በጠንካራ ቃላት ታጅበው የተቹት አቶ መላኩ” የአስመራጭ ኮሚቴ ሰብሳቢ እንበለው መድረክ መሪ ደስታ ለማብሰር የጓጓ እንጂ በገለልተኝነት ምርጫ የሚመራ አይመስልም”በማለት ተናግረዋል። አቶ መላኩ ከኢንጂነር ቶኪቻ ጋር ስለነበራቸው አጠር ያለ ቆይታ ሲናገሩ” አንደኛው ዕጩ ኢንጂነር ቶኪቻ ከምርጫው በፊት ውጤቱን ያወቁ ይመስላሉ ከቆይታዬ የተረዳሁት እንደሱ ነው ኬንያዊው የኛ ሀገር ቴክኖሎጂ ሄዷል እኛ ሀገር በ20 ደቂቃ የምርጫው ውጤት ይታወቃል ሲል ኢትዮጵያዊው ደግሞ የእኛ ሀገር ከናንተ ይሻላል ምርጫው ከመካሄዱ በፊት አሸናፊው ይታወቃል አለ ብለው የነገሩኝ እንደኔ ማን እንደሚያሸንፍ ቀድመው እንዳወቁ አስረድቶኛል” ሲሉ የነበረውን ሂደት ገልጸዋል።
አቶ ኢሳያስ 94 ድምጽ እሳቸው 27 ኢንጂነር ቶኪቻ 17 ድምጽ እንደሚያገኙ ቀድሞ የተሰራና ፖለቲካዊ ውሳኔ ውጤት እንደሆነ የሚናገሩት አቶ መላኩ” በገንዘብ ያልተታለሉና ፖለቲካዊ ማስፈራሪያውን ያልፈሩ 27 መራጮቼ መመስገን አለባቸው ሀገርን በገንዘብና በፖለቲካዊ ጫና ማዳን አይቻልም የመረጡትም ቢሆን ተገደው እንጂ እኛን እንደሚደግፉ እናውቃለን ከምርጫው በኋላ ተገደን ነው ሶሪ አግባብ አልነበረም ያሉን መራጮች ነበሩ ዛሬ ተዳፍኖ ፍርሃት ተፈጥሮ ይሆናል እነሱንም እንረዳለን ነገ ግን በቀጣይ አመታት ከ27 ምክንያታዊ መራጭ ሙሉ ጉባኤው እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ አስረድተዋል። አቶ መላኩ የምርጫው ዕለት የመጨረሻ ግብዣ በመዝገበ ስጋ ቤት ተፈጸመ” ሲሉም አስረድተዋል።