በካሜሮን አስተናጋጅነት ለሚካሄደው ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለማለፍ በዝግጅት ላይ
የሚገኘውና አስቀያሚ ጅማሮ ለማሳየት የቻለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለሁለት ተከታታይ
የውድድር ዓመታት ተሳታፊ ከሆነበት የቻን ውድድር ውጪ ለመሆን መብቃቱ የእግር ኳሳችንን
እንዴትነት በበለጠ መልኩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ስለመሆኑ እንድንገነዘብ ያበቃን መሆኑን የምታምነው
ሀትሪክ… የውጤቱ ከዜሮ በታች የመሆንና የብሔራዊ ቡድኑ አቋም መዝቀጥ ሳይሆን ከአሰልጣኙ
ጋር የተጀመረው እሰጥ እገባ ቀልብ እንዲስብ የተደረገበት ሁኔታ አስደማሚ ለመሆን መብቃቱን
ከመግለፅ ወደ ኋላ አትልም፡፡
የአፍሪካ ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታን ከሜዳው ውጪ በማድረግ በጋና ብሔራዊ ቡድን 5ለ0
በሆነ “ታሪክ” ተብሎ ሊረሳ በተቃረበ ሰፊ ውጤት ለመሸነፍ መብቃቱን ተከትሎ ብዙ አስተያየቶች
ከመደመጣቸው ባሻገር አስቀድሞ ከአሰልጣኙ ሲደመጥ የነበረው “ከምድባችን እናልፋለን” የሚለው
አቋም መቀጠሉ ይዋል ይደር እንጂ መጨረሻውን እናያለን ብለው ቀጠሮ ለመያዝ ከቻሉ የስፖርት
ቤተሰቦች መካከል አንዷ የነበረችው ሀትሪክ.. ብሔራዊ ቡድናችን በጀመረው የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ
ማጣሪያ ላይ ሁለተኛውን ጨዋታውን ሳያከናውን በአቅሙ የተሰራ በመሰለው የቻን ውድድር ላይ
ተሰፍሮና ተለቅቶ ገለባ ለመሆን መቻሉ የቡድናችንን የት ደረሴነት ቅርብ አደር ከመሆን እንደማይዘል
ገና በጊዜ ሊያረጋግጥልን መብቃቱን ተገንዝባለች::
የማጣሪያ ሂደቱ በዞን ተከፋፍሎ የሚካሄድበትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እንደሌሎች
ማጣሪያዎች ሁሉ ጠንካራ ተብለው የሚጠሩት የሰሜንና የምዕራብ አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች
አብረውን በማይደለደሉበትና እንደኛው ሁሉ ተመጣጣኝ አቅም ካላቸው የምስራቅና መካከለኛው
የአፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች አብረውን በሚደለደሉበትና እንደኛው ሁሉ ተመጣጣኝ አቅም ካላቸው
የምስራቅና መካከለኛው አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች በሚሳተፉበት የማጣሪያ ጨዋታ ተሳታፊ በመሆን
የቻን ውድድር ጉዞውን ለማካሄድ የሚችልበት አቅም ማጣቱ አንገት የ ሚያስደፋ ለመሆን መብቃቱን
የተከታተለችው ሀትሪክ… አሁን ያለው ብሔራዊ ቡድናችን ባለፉት ሁለት ተከታታይ የቻን ውድድሮች
ላይ የያዘንነውን የተሳተፍ ጉዞ ተግባራዊ ለማድረግ ያልቻለበት እውነታ ያለምንም ጥርጥር ልክ የለሽ
ከሆነ ድክመት ጋር የሚያያዝ ብቻ መሆኑን እንደማትክደው ታረጋግጣለች፡፡
በአገራችው ሊግ ውስጥ የሚጫወቱ ተጨዋቾች ብቻ በሚሳተፉበት የማጣሪያ ሂደት የተሻለ ሆኖ
ለመታየት አለመቻሉ በራሱ “ከዚህ በላይ የተሻለ አድል ምን ሊመጣ ነው?” የሚል ጥያቄ ከሚያቀርቡ
ወገኖች ጋር በመሆን ጥያቄውን አጉልታ የምታሳየው ሀትሪክ… የብሔራዊ ቡድኑን የአሰልጣኝነት
ወር ተራ የተረከቡት የአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስብስብ ይሄንን የተሳተፎ መንገድ ለሶስተኛ ጊዜ
ለማሳካት አለመቻሉ ውድቀት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም ከተመዘገበው ደካማ ውጤት ይልቅ
በእሣቸውና በፌዴሬሽኑ መካከል የተመዘገበው “የእለቃለሁ፤ አትለቅም” አኩኩሉ ጎልቶ ለመታየት
መቻሉና ሰፊ ሽፋን ለማግኘት መብቃቱ ለተፈጠረው የውጤት ርቀት የተጠያቂውን ደብዛ ለማሸሽ
እንደተደረገ የአቅጣጫ ማስቀየሻ ስልት አድርጋ ልትቆጥረው መብቃቷን ለማረጋገጥ ትወዳለች፡፡
በከፍተኛ ወርሃዊ ክፍያ ብሔራዊ ቡድኑን የማሰልጠን ኃላፊነት የተረከቡት አሰልጣኝ አሸናፊ
በቀለ የአሰልጣኝነት ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ በሰጡት ማብራሪያ ላይ በቀጣዩ ውድድር “በአፍሪካ
ዋንጫ ሩብ ፍፃሜ እንደርሳለን” የሚል ቀልድ የሚመስል አቋማቸውን ሲያስተጋቡ በወቅቱ ትዝብቷን
በግልፅ አስቀምጣ እንደነበረች የማትዘነጋው ሀትሪክ… ገና በማጣሪያው የመጀመሪያ ጨዋታ
የገጠማቸው የ5ለ0 ውጤት በቅርብ በአልጄሪያ ብሔራዊ ቡድን ከገጠመን ሽንፈት ጋር ተደምሮ
“ታሪክ” ሆኖ የቀረውን በብዙ ግብ የመሸነፍ ባህል እንዲመለስ ያደረገ ሆኖ መታየቱ የፈጠረውን ክፉ
መንፈስ የተሰወረ አለመሆኑን ታረጋግጣለች፡፡
አሰልጣኙ ብሔራዊ ቡድኑን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ሙሉ ጊዜያቸው ብሔራዊ ቡድኑን
በማሰልጠንና ለውጤት በሚያበቃ ስራ ተጠምደው ስለመታየታቸው ብዙም የተጨበጠ ነገር እንደሌላት
የምትገልፀውና የተጠናከረ ስራ ከመስራት ይልቅ በተቃራኒው “አሰልጣኝነቴን እለቃለሁ፤ አትለቅም”
በሚለው እሰጥ እገባ ተጠምደው ጉልበታቸውን ሲጨርሱ ለመታየት መብቃታቸውን የምትታዘበው
ሀትሪክ… ወቅታዊው አሰልጣኝ ከሳቸው በፊት የነበሩት አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻውና አሰልጣኝ ዮሐንስ
ሳህሌ አረረም መረረም ማሳካት የቻሉትን የቻን የተሳትፎ ጉዞ ለማሳካት አለመብቃታቸው በቀጣዩ
ጉዟቸው ላይ የጥያቄ ምልክት እንዲቀመጥ ማስገደዱን አትክድም፡፡
የቻን ውድድር እንደ ኢትዮጵያ ለመሰለው በእግር ኳስ ደረጃቸው ደካማ ለሆኑ አገሮች በልክ
የተሰፋ እጀ ጠባብ ውድድር ከመሆኑ አንፃር ከሁለት ተጨዋቾቿ በስተቀር ሙሉውንና ቋሚውን
ብሔራዊ ቡድኑን ይዞ ለሚወዳደረው ብሔራዊ ቡድናችን ተሳትፎ ብቻውን የመጨረሻ ግብ ሊሆን
እንደማይገባው የምታምነው ሀትሪክ… ብሔራዊ ቡድናችን በውድድሩ ላይ ከተሳትፎ በዘለለ የዋንጫ
አሸናፊ መሆን በሚጠብቅበት በዚህ ውድድር ገና በማጣሪያው ተሸንፎ ከተሳትፎ ውጪ ለመሆን
መቻሉ ስሜት የሚነካ ብቻ ሣይሆን በብሔራዊ ቡድኑም ሆነ በስልጠና ሂደቱ ላይ አስቀድሞም ቢሆን
የያዘችውን ተቃውሞ አጠናክራው እንድትቀጥል የሚያደፋፍር መሆኑን ታረጋግጣለች፡፡
“በአፍሪካ ዋንጫ ውድድር ለሩብ ፍፃሜ እንደርሳለን” ብለው ገና ከመነሻው በድፍረት የተናገሩትና
ከጋናው ሽንፈት በኋላም ቢሆን “ለአፍሪካ ዋንጫ የማለፍ ተስፋ አሁንም በእጃችን ነው” በማለት
በድጋሚ የተናገሩት አሰልጣኝ አሽናፊ በቀለ ይሄንን አቋም በተደጋጋሚ ጊዜ ለማንፀባረቅ የቻሉት
“ምን ሰርተው? ምንስ ይዘው?” የሚል ጠንካራ ጥያቄ ከማስነሳቱም ባሻገር፤ “ምላሹን ጊዜ ይሰጠዋል”
የሚል የጋራ መግባቢያ ላይ እንዲደርስ ማብቃቱን የ ማትዘነጋው ሀትሪክ…. ይሁንና የአሰልጣኙን
ተደጋጋሚ አቋም ለማረጋገጥ ቀጣዩን የአፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ መጠበቅ አስፈላጊ ሳይሆን በቻን
የማጣሪያ ጨዋታ ምላሹን ለማግኘት ማብቃቱን ትረዳለች፡፡
አሰልጣኙ ቀደም ሲል “ለሩብ ፍፃሜ እደርሳዋለው” በኋላ ላይ ደግሞ “ለተሳተፎ አበቃዋለው”
ያሉት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከቻን ውድድር ውጪ በመሆኑ የትም እንደማይደርስ ለማሳየት
መብቃቱን የምታምነው ሀትሪክ… ከዚህ ባሻገር ምንም የሚታይና የሚዳስስ ውጤት ሳያስመዘግቡ
“ለሩብ ፍፃሜና ለተሳትፎ አበቃዋለው” ያሉትን ብሔራዊ ቡድን ጥለው ለመጓዝ “እለቃለው፤
አትለቅም” ወደ ሚል ዝቅታ ለመውረድ መቻላቸውን ልትታዘበው መብቃቷን ታረጋግጣለች፡፡
አሰልጣኙ ብዙም ሳይጓዙ ገና በማለዳው ባስመዘገቡት ውጤት ኃላፊነታቸውን ለመልቀቅ ጫፍ
መድረሳቸውና የሚዲያ ፍጆታ ሆነው የከረሙበት ጉዳይ የፌዴሬሽኑ ሰዎች በገነቡት ቡድን ላይ
እምነት እንደሌላቸው የሚያረጋግጥ መሆኑን የምትገልፀው ሀተሪክ… የፌዴሬሽኑ አመራሮች ከዚህ
ቀደም አሰልጣኙን “ለቻን ጨዋታ ይሄ ሁሉ ተጨዋች መርጦ መዘጋጀት ምን ያስፈልጋል? ባሉት
ተጨዋቾች ውድድሩን መወጣት ትችላለህ” ሲሉ የሰጡትን አስተያየት እንደጣልቃ ገብነት ቆጥረው
ራሣቸውን ነፃ ለማድረግ የመረጡበት መንገድ ሊሆን እንደሚችል ይታመናል፡፡
ምንም እንኳን በአሰልጣኙ የአሰራር ነፃነት ጣልቃ መግባት የሚደገፍ ባይሆንም፤ የፌዴሬሽኑ
አመራሮች በሰጡት አስተያየት ግን እንደምትስማማ የምታምነው ሀትሪክ… ከሱዳን ብሔራዊ ቡድን
ጋር በተደረገው ጨዋታ በታየው ብሔራዊ ቡድን አቋምና በአሰልጣኙ ላይ እምነት ያጡት አመራሮች
የሰጡት አሰተያየት ከሀቅ የመነጩ እንደሆኑ አትክድም፡፡
የፌዴሬሽኑ አመራሮች ቀደሞውኑም ቢሆን አሰልጣኙን ሲመርጧቸው በክለብ አሰልጣኝነታቸው
ለተከታታይ አመታት ጠንካራ ተፎካካሪ ቡድን ገንብተዋል በሚል አቋም መሆኑን አስቀድመው
በመቃወም ትክክል እንዳልሆነ ደጋግማ የገለፀችው ሀትሪክ… አራተኛና አምስተኛ በመውጣት የታወቀ
ክለብን ማሰልጠን ለብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝነት የሚያስመርጥ ከሆነ የብሔራዊ ቡድኑ ደረጃ ዝቅ
ብሏል የሚል ዕምነት እንዲያድርባት ያስገደደ መሆኑን አበክራ ትገልፃለች፡፡
አሁን ባለው እውነታ መልቀቂያ የጠየቀውም ሆነ የተጠየቀውም ማለትም ሁለቱም አካላት
ሚዛን የሚያነሱ እሰጥ እገባ ውስጥ መገኘታቸውን የምትረዳውና ሁለቱም አካላት የስህተቱ
ባለቤቶች ከመሆናቸውም በላይ ፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ቡድኑን አልጣኝነት በኮታ የማዳረስ ተግባር
ላይ ትኩረት ሰጥቶ ለመስራት መፍቀዱን ሁሉም የስፖርት ቤተሰብ የተከታተለው ሀቅ ለመሆን
እንደበቃ የምትገልፀው ሀትሪክ.. አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ በክለብ አሰልጣኝነታቸው ከዋንጫ ጋር
የሚነሳና ለብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት የሚያበቃ ውጤት ባለቤት ስለመሆናቸው የሚገልፅ መረጃ
ሳይገኝ በቴክኒክ ኮሚቴው የኮታ ድልድል መሠረት እድሉን ለማግኘት የበቃበት አካሄድ ለመፍጠር
መቻሉን ታምናለች፡፡
ካለው አጠቃላይ እውነታ በመነሳት ከቻን ውድድር መውጣታቸውን የሚጠበቅና ብዙም
የሚያስገርም እንዳልሆነ የምታምነውና አሰልጣኙ የያዙትን የብሔራዊ ቡድን ኃላፊነት ቢለቁም
ባይለቁም ምንም የተለየ ነገር እንደሌለው የምታምነው ሀትሪክ… ውጤት ሲጠፋ የተፈጠረውን
ይሄንን መሰሉን አቅጣጫ የማስቀየሻ አጀንዳ ብዙም ማራገብ አስፈላጊ እንዳልሆነ በማመን በአጭሩ
አሰልጣኙ ያቀረቡትን ጥያቄ ፌዴሬሽኑ ያለምንም ማመንታት በመቀበል ስሀተቱን ማረም የሚጠበቅበት
መሆኑን ታስገነዝባለች፡፡