በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ እና ከነገ በስቲያ ሲቀጥሉ ነገ (ቅዳሜ) 3 ጨዋታዎች እንዲሁም ከነገ በስቲያ (እሁድ) 5 ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል።
ነገ በተመሳሳይ 9 ሰዓት ላይ አዲግራት ላይ ካደረጋቸው 2 ጨዋታዎች ሁለቱንም በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲዳማ ቡናን ሲያስተናግድ በሼህ መሀመድ ሁሴን አሊ አላሙዲን ስታድየም ወልድያ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ ይጫወታሉ። ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ዝግጅት 3 ተጫዋቾችን በማስመረጡ ምክንያት ምንም የሊጉን ጨዋታ ማከናወን ያልቻለው ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ሳምንት ሳይጠበቅ ሜዳው ላይ በወላይታ ድቻ የ1-0 ሽንፈት ያስተናገደውን መከላከያን 11:30 ሲል አ/አ ስታዲየም ላይ ያስተናግዳል።
ፕሪምየር ሊጉ እሁድ ሲቀጥል 4ጨዋታዎች በተመሳሳይ 9 ሰዓት ሲደረጉ ቅ/ጊዮርጊስ መቐለ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ 11:30 ላይ ይደረጋል። ካደረጋቸው 2 ጨዋታዎች ሁለቱንም በአቻ ውጤት ያጠናቀቀው አርባምንጭ ከተማ 1 ነጥብ ያለውን ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ያስተናግዳል። በጅማ ስታዲየም 3 ነጥቦችን ይዞ በሊጉ 3ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ጅማ አባጅፋር 1 ነጥብ ይዞ በሊጉ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘውን ፋሲል ከተማ ሲያስተናግድ ቦዲቲ ላይ የሊጉ መሪ ወላይታ ድቻ 1 ነጥብ ያለውን አዳማ ከተማን ያስተናግዳል። እዚህ አ/አ ላይ በ9፡00 በሁለተኛው ሳምንት ወደ አዳማ ተጉዞ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለግብ አቻ ተለያይቶ የተመለሰው ደደቢት በሁለተኛው ሳምንት ወልድያ ከተማን በሰፊ ውጤት ያሸነፈውን ሐዋሳ ከተማን ያስተናግዳል። 11:30 ሲል እንደ ኢትዮጵያ ቡና ሁሉ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቻን ዝግጅት 10 ተጫዋቾችን በማስመረጡ ምክንያት ምንም የሊጉን ጨዋታ ማከናወን ያልቻለው የአምናው ሻምፒዮን ቅ/ጊዮርጊስ አዲስ አዳጊውን መቐለ ከተማን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል።
ፕሪምየር ሊጉን ወላይታ ድቻ በ4 ነጥቦች ሲመራ ምንም ጨዋታ ያላደረጉት ኢትዮጵያ ቡና እና ቅ/ጊዮርጊስ የሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።