የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት የዕለተ ቅዳሜ ጨዋታ ቅድመ ዳሰሳ
በኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ቀሪ 7 ጨዋታዎች ቅዳሜ እሁድ እና ሰኞ በሚደረጉ ጨዋታዎች ይቀጥላሉ። የሊጉ 1 ጨዋታ ባሳለፍነው ሀሙስ በቅ/ጊዮርጊስ እና ጅማ አባጅፋር መካከል ተደርጎ በቅ/ጊዮርጊስ 3-0 አሸናፊነት መጠናቀቁ ይታወሳል።
አ/አ ላይ በሚደረገው በቅዳሜ ብቸኛ የሊጉ ጨዋታ 10፡00 ሲል ኢትዮ-ኤሌክትሪክን ከ አዳማ ከተማ የሚያገናኝ ይሆናል።
በውጤት ቀውስ ውስጥ የሚገኘው እና በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን ካሰናበተ እና የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩትን አሸናፊ በቀለን ከቀጠረ በኋላ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታው ይሆናል። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የሊጉ ጅማሬ ላይ ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ ችሎ የነበረ ቢሆንም ከጨዋታ ጨዋታ እየወረደ በመምጣት የሊጉ ግርጌ ላይ ከሚገኘው አርባምንጭ ከተማ በ2 ነጥቦች ብቻ ከፍ ብሎ 15ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ የሚመራው አዳማ ከተማ በአንፃሩ በተከታታይ ያጋጠሙት ነጥብ መጣሎች አሰልጣኙን ጫና ውስጥ ከቷቸዋል።
በ9ኛው ሳምንት ወደ ሶዶ አቅንቶ ወላይታ ድቻን የገጠመው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በወላይታ ድቻ 2-0 ሽንፈትን አስተናግዶ ሲመለስ አዳማ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው ሲዳማ ቡናን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት መለያየቱ ይታወሳል።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል በዘንድሮው የወድድር አመት አጥቂው ቢኒያም አሰፋ በተደጋጋሚ ጉዳት ማስተናገዱ እንዲሁም ሌላው አጥቂ ዲዲዬ ሊብሬ ወጥ አቋም ማሳየት አለመቻሉ እና የግብ ጠባቂ ችግር ቡድኑን ሲጎዱት በግልፅ ተስተውሏል። ከዚህ ባሻገር ከመሀል ሜደ እየተነሳ ግብ በማስቆጠር ከጅማ አባጅፋሩ አጥቂ ኦኪኪ አፎላቢ ጋር የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ የሚገኘው ካሉሻ አልሐሰን ሚና ግን ሳይነሳ መታለፍ የለበትም። በአዳማ ከተማ በኩል የአጥቂው ሚካኤል ጆርጅ መጎዳት ተከትሎ የቡድኑ የማጥቃት እና ግብ የማስቆጠር ሀላፊነት በዳዋ ሁቴሳ ትከሻ ላይ ወድቋል። ይህ የቀድሞ የቅ/ጊዮርጊስ ተጫዋች ባለፉት 2ጨዋታዎች ላይ 2ግቦችን በማስቆጠር ሀላፊነቱን በአግባቡ እየተወጣ እንደሆነ ማሳየት ችሏል።
አዳማ ከተማ ካደረጋቸው 9ጨዋታዎች 5ቱን ከሜዳው ውጪ ያደረገ ሲሆን ዛሬ ወደ አ/አ ተጉዞ የሚያደርገው ጨዋታ 6ኛ ከሜዳው ውጪ የሚያደርገው ጨዋታ ይሆናል፡፡ አዳማ ከተማ ካደረጋቸው 5 ጨዋታዎች ወደ ሶዶ ተጉዞ ወላይታ ድቻን ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው ከሜዳው ውጪ ያስመዘገበው ድል ሆኖ ተመዝግቦለታል። 1 ጨዋታ ማለትም በወልድያ ስፖርት ክለብ የተሸነፈ ሲሆን ከመከላከያ ጋር አ/አ ስታዲየም እንዲሁም ድሬ ላይ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር በተመሳሳይ ያለ ግብ 0-0 መቐሌ ላይ ከመቐሌ ከተማ ጋር ደግሞ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በአንፃሩ በሜዳው 5 ጨዋታዎችን የተጫወተ ሲሆን ካደረጋቸው 5 የሜዳው ላይ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ቡናን 2-1 በሆነ ውጤት ያሸነፈበት ጨዋታ ብቸኛው በሜዳው ያስመዘገበው ድል ነው። በወልዋሎ አ.ዩ. እና በደደቢት በተመሳሳይ 3-1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ከመከላከያ ጋር 1-1 እንዲሁም ከጅማ አባጅፋር ጋር 0-0 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል።
በአጠቃላይ በፕሪሚየር ሊጉ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ማድረግ ከሚገባው 9ጨዋታዎች 8ቱን አድርጎ 2ጨዋታዎችን አሸንፎ በ4 አቻ ተለያይቶ 2ቱን ተሸንፎ 8 ነጥቦችን ሰብስቦ 15ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ አዳማ ከተማ በአንፃሩ 9ጨዋታዎችን አድርጎ 2ጨዋታዎችን አሸንፎ 6ጨዋታዎችን አቻ ወጥቶ 1ጨዋታ ተሸንፎ ማግኘት ከሚገባው 27ነጥቦች 12ቱን አሳክቶ ከመሪው ደደቢት በ7ነጥቦች ርቆ 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል።
ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል አወት ገ/ሚካኤል ዘካሪያስ ቱጂ ቢኒያም አሰፋን እና ሀይሌ እሸቱን በጉዳት ሲያጣ ከወላይታ ድቻ ጋር ሲጫወቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ የተሰናበቱትን ተስፋዬ መላኩንና በሀይሉ ተሻገርን በቅጣት አያገኝም፡፡ አዳማ ከተማ በኩል ሱለይማን መሀመድ አዲስ ህንፃ እና ረዘም ላለ ጊዜ ከሜዳ የሚያርቅ ጉዳት የገጠመው አጥቂው ሚካኤል ጆርጅ በጨዋታው ለአዳማ ከተማ ግልጋሎት የማይሰጡ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ሌላው ጉዳት ላይ የነበረው ተጫዋች ቡልቻ ሹራ ከጉዳቱ አገግሞ ልምምድ የሰራ ሲሆን የመሰለፍ እና ያለመሰለፉ ጉዳይ ገና አለየለትም፡፡
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አ/አ ስታዲየም ላይ 10፡00 ሲል የሚጀምር ይሆናል።