በስምንተኛው ሳምንት የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ቀን ሁለተኛ ጨዋታ ኢትዮጵያ መድን ሲዳማ ቡናን 4ለ0 በሆነ ዉጤት ማሸነፍ ችሏል።
በእንቅስቃሴ ረገድ ተመጣጣኝ በነበረዉ የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ሲዳማ ቡና በመስመር እና ረጃጅም ኳሶች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመግባት ሲጥሩ በተመሳሳይ የገ/መድህን ሀይሌዉ ኢትዮጵያ መድን የሜዳዉን የመሐል ክፍል ተቆጣጥረዉ በመጫወት ብልጫ ለመዉሰድ ሲጥሩ ተስተውሏል።
በተለይ በ10ኛዉ ደቂቃ ላይ የሲዳማ ቡናዉ አምበል ፍሬዉ ሰለሞን በቅጣት ምት የሞከራት ኳስ የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ ስትሆን በድጋሚ በ22ኛዉ ደቂቃ ላይ ተከላካዩ ያኩቡ ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ በጭንቅላቱ በመግጨት ቢሞክርም ግብ ጠባቂዉ አቡበከር ኑሪ በድንቅ ብቃት ኳሷን አዉጥቷታል።
- ማሰታውቂያ -
በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም በጥቂቱም ቢሆን በሙከራ ረገድ በሲዳማ ቡና ብልጫ የተወሰደባቸው የሚመስሉ የነበሩት መድኖች መሪ መሆን የቻሉበትን ግብ በፍፁም ቅጣት ምት ማግኘት ችለዋል።
በ37ኛዉ ደቂቃ ላይ ኪቲካ ጀማል ያሻማዉን ኳስ ተከላካዩ ያኩቡ ካማራ በዕጁ በመንካቱ ምክንያት የተገኘዉን ፍፁም ቅጣት ምት ሀብታሙ ሸዋለም ወደ ግብነት ቀይሮ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።
በ41ኛዉ ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተሻማዉን ኳስ ተከላካዮች ሲመልሱት ከሳጥን ዉጭ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኝ የነበረዉ አማካዩ ዮናስ ገረመዉ በቀጥታ ኳሷን ወደ ግብ በመላክ አስደናቂ ግብ ማስቆጠር ሲችል ክለቡም ጨዋታዉን 2ለ0 እንዲመራ ማድረግ ችሏል።
45ኛዉ ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂዉ መክብብ ደገፉ ሲሞን ፒተር ላይ ጥፉት መስራቱን ተከትሎ በቀይ ካርድ ከሜዳ ሲወገድ በምትኩ ሶስተኛ ግብ ጠባቂ የሆነዉ አዱኛ ፀጋየ ወደ ሜዳ ቢገባም የብሩክ ሙሉጌታን የፍፁም ቅጣት ምት ኳስ ማዳን ሳይችል ቀርቶ አጋማሹ በመድን 3ለ0 መሪየት ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ የአሰልጣኝ ገ/መድህን ሀይሌዉ ቡድን የማጥቃት ሀይሉን አጠናክሮ ወደ ሜዳ ሲመለስ በተቃራኒው ሶስት ለዜሮ እየተመራ ወደ መልበሻ ክፍል አምርቶ የነበረዉ ሲዳማ ቡና ወደ ራሱ የግብ ክልል አፈግፍጎ በመጫወት የግብ መጠኑ ከዚህም በላይ እንዳይሆን ሲጥሩ ተስተውሏል።
ነገር ግን ሲዳማ ቡና ምንም እንኳን የቁጥር ብልጫ ቢወሰድበትም በመልሶ ማጥቃት ጥሩ ጥሩ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችሎ ነበር ፤ በዚህም በመልሶ ማጥቃት በተገኘ ኳስ 55ኛዉ ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ላይ ተከላካዩ ቴዎድሮስ ጥፉት በመስራቱ የተገኘዉን ኳስ ፍሬዉ ሰለሞን ቀጥታ ወደ ግብ ቢልክም የግብ ዘቡ አቡበከር ኑሪ ተቆጣጥሯታል።
በ60ኛዉ ደቂቃ ላይ ደግሞ በቀኝ መስመር በኩል ከይገዙ ቦጋለ የተቀበለዉን ኳስ ፀጋየ አበራ በቀጥታ ወደ ግብ ሞክሮ የነበረ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት ወደ ዉጭ ወጥታለች።
በ65ኛዉ ደቂቃ ላይ ግን መድን ተጨማሪ ግብ ማስቆጠር ችሏል። በዚህም በያኩቡ ካማራ እና በግብ ጠባቂዉ አዱኛ ፀጋየ አለመግባባት የተገኘችዉን ኳስ በቅርበት የነበረዉ ኪቲካ ጀማል በቀላሉ ወደ ግብነት ቀይሮ የክለቡን መሪነት ወደ አራት ለዜሮ ከፍ ማድረግ ችሏል።
የጨዋታው ሰዓት እየገፋ በመጣ ቁጥር ሲዳማ ቡና በቡልቻ ሹራ ፣ ይገዙ ቦጋለ እና ፍሬዉ ሰለሞን አማካኝነት በተደጋጋሚ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን ማድረግ ቢችሉም አንድም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ቀርተዋል። በአንፃሩ በዕለቱ እንደ ቡድን ድንቅ የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ጨዋታዉን በፈለጉት መንገድ በመቆጣጠር 4ለ0 በሆነ ዉጤት ሲዳማ ቡናን መርታት ችለዋል።