የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ሞሮኮ ላይ የተደረጉትን ሁለት የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎችን አስመልክቶ በዛሬው ዕለት በፌዴሬሽኑ ፅህፈት ቤት ከጋዜጠኞች ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል ።
አስቀድመው በቀዳሚው ጨዋታ ስለነበረው አየር ሁኔታ የተናገሩት አሰልጣኝ ገብረመድኅን ጨዋታው እንዲቋረጥ ብንጠይቅም ፊፋ እንዲቋረጥ አይፈልግም የሚል መልስ ነው የተሰጠን ብለዋል ።
“የአየር ሁኔታው በየጊዜው ይለያያል ። ርጥበት አዘል የአየሩ ሁኔታም አንዴ ይወጣል አንዴ ይመለሳል ። ነገር ግን እኛ የነበረው ሁኔታ ቀዝቃዛ አየር እንደነበረ እናውቃለን ። እንዳያቹት አየሩ አንዴ ይወጣል አንዴ ይመለሳል ። ሁኔታውን አይተነዋል ግን ምንም መቀየር የምንችልባቸው ሁኔታዎች አልነበሩም ። ”
- ማሰታውቂያ -
“በተጨባጭ ቢታይም በተደጋጋሚ ጥያቄዎች አቅርበናል ። ነገር ግን ፊፋ እንዲቋረጥ አይፈልግም የሚል ድርቅ ያለመልስ ነው የተሰጠን ። ”
“በተለይም ሁለተኛው አርባ አምስት ደቂቃ ላይ አስቸጋሪ ነበር ። ከኛ በተቃራኒ በካታንጋ አቅጣጫ ማለት ነው የኛንም የተቃራኒ ቡድን ተጫዋቾችን ለይተን የማናይባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።”
የመጀመሪያው ጨዋታ ደመናማና ቀዝቃዛ ነው ያሉት ገብረመድህን ኃይሌ ሁለተኛው ጨዋታ ደግሞ ፀሐይና ሞቃታማ የአየር ሁኔታ የነበረው መሆኑን በማንሳት የአየር ሁኔታ ለውጥ በተወሰነ መልኩ በቡድኑ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ሲሉ ተናግረዋል ።
ከቡርኪናፋሶ ብሔራዊ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታ ላይ ካለው የደረጃ ልዩነት ጋር በተያያዘ አስቀድመው በልምምዶች ወቅት እና ቁጭ ብለው በመነጋገር በስነ ልቦና ደረጃ እንዲዘጋጁ እና ጫና እንዳይኖርባቸው ባደረጉት ጥረት የጠበቁትን ነገር ግን እንዳላዩ ተናግረዋል ።
“በመጀመሪያዎቹ 70 ደቂቃዎች ጥሩ ነበርን በመጨረሻዎቹ 20 ደቂቃዎች ግን የጠበቅነው ያህል አልነበረም ። ጎል ካስተናገድን በኋላ ማለት ነው ። ለጨዋታው በጥሩ ዝግጅት ገብተናል ። ጎል እስካስተናገድንበት ጊዜ ድረስ በጣም በጥሩ ሁኔታ በብቃት የተቆጣጠሩበት ሁኔታ ነበረ ።”
” ከተጋጣሚም በተሻለ አጥቅተናል ። በተለይም በመልሶ ማጥቃት ብዙ ኳሶች ነጥቀን ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ገብተን ጎል ለማስቆጠር አጋጣሚዎች ሁሉ ተፈጥረው ነበረ ። አጨራረስ ላይ ግን ጥሩ አልነበረም ። ”
አሰልጣኙ አክለውም የነበረውን የስነ ልቦና ጫና በአጭር ጊዜ መቅረፍ አይቻልም ብለዋል ።
ተጋጣሚን ኳስ በመንጠቅ በፍጥነት ለማጥቃት አስበው እንደነበረም በመናገር ተጋጣሚ እስኪደራጅ የነበሩ መዘግየቶች ግን ዋጋ እንዳስከፈላቸው ተናግረዋል ።
ስለአጨዋታቸው የተናገሩት አሰልጣኙ ለመከላከል አልገባንም ሲሉ ተናግረዋል ። “እኛ ለመከላከል አልገባንም ። ያለው ደረጃችንን እናውቀዋለን ። ግን ደሞ እኛ እንደ ቡድን ተንቀሳቅሰን እናሸንፋለን የሚል ዕምነት ነበረን ። አቀራረባችንም ለማሸነፍ ነበር ።
“ግን ወደ መጨረሻ አካባቢ አንድ ጎል ብቻ አይደለም ሶስት ጎሎች አስተናግደናል ። ግን ይሄ የተፈጠረው በግል በተፈጠሩ ስህተቶች ነው ። እንጂ እንደ ቡድን ብልጫ ወስደውብን አልነበረም ።”
እንደ ግል የነበረውን ስህተት ለማስተካከል እንደማይከብድ የተናገሩት አሰልጣኙ እንደ ቡድን ቢሆን ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል ብለዋል ።
በሜዳ ላይ መጫወት ያለውን ጠቀሜታ ያነሱት አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ምናልባት ጨዋታዎቹ እዚህ ተደርገው ቢሆን ኖሮ ቢያንስ ማግኘት ከሚጠበቅባቸው ስድስት ነጥቦች አራት ማግኘት ይችሉ እንደነበር ተናግረዋል ።
ስለ አጨዋወት ለውጣቸው በሰጡት አስተያየትም እዚሁ ተጫውትንም ሌላ ሀገር ላይ በዚህ አጨዋወት እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ።
አክለውም የአጨዋወት ለውጡ በተጫዋቾቹ ላይ ግርታን አልፈጠረም ብለዋል ።
በተጨማሪም ስለ ፊት መስመር አጥቂ ምርጫቸው ለተነሳላቸው ጥያቄ በሀገሪቱ ያለው የዘጠር ቁጥር ሚናን በብቃት የሚወጣ ተጫዋች ዕጥረት አለመኖሩ እንዲቸገሩ እንዳረጋቸው ተናግረዋል ።
“ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ዘጠኝ ቁጥር ተጫዋቾች አሉ ለማለት በግሌ አያስደፈረኝም ። ግን ያሉትን ዘጠኝ ቁጥሮች ወደፊትም ወስደን ማየት ይጠበቅብናል ። ነገር ግን ሌላ አማራጭ መውሰድ እንደሚጠበቅብኝ አስባለሁ ። በዛ ቦታ ላይ ሌላ ሰው ማለማመድ አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ። ምክንያቱም ያላቸው ቴክኒካል አቅም ፤ የአጨራረስ አቅማቸው ፤ የታክቲክ አረዳዳቸው ብንመለከት በየክለቦቹ የሚገኙት የዘጠኘ ቁጥሮች ሁኔታ ለብሔራዊ ቡድን አስቸጋሪ ነው።”
ወደፊት ባሉን ጊዜዎች ሰፊ ነገሮትን እንሰራለን ያሉት አሰልጣኙ በታዳጊዎች ላይ ለመስራት ያሰቡትን እቅድ ተናግረዋል ። “ለውጥ ማምጣት ከተፈለገ ብዙ ነገሮችን ማየት አለብን ። የትውልድ አንድ ቦታ ላይ የመቆም ነገር ይታየኛል ስለዚህ ወጣቶችን የምናመጣበት መንገድም አንድ ነገር ነው ።”
“ስለዚህ ለፌዴሬሽኑ በቅርቡ የማስገባው ዕቅዱ ይኖራል ። ከ23 አመት በታች ያሉ ወጣት ተጫዋቾችን መልምሎ እንደ “ሻዶው” ቡድን ለማዘጋጀት ሀሳቡ አለኝ ። ”
“የሊጉ ውድድር የሚደረግበት አንድ ቦታ ስለሆነ ከፕሪሚየር ሊግ የሚመረጡ ተጫዋቾች በተለይ ከተቻለ በሳምንት አንድ ቀንም ክለቦች ፈቃደኛ ከሆኑም በሳምንት ሁለት ቀን የምናሰራበትና በተወሰነ ከአጨዋወት ዘይቤው ጋር የመተዋወቂያ መድረክ እንዲኖራቸው ለማብቃት ማለት ነው ።”
“አሁን የተወሰኑ ብቅ እያሉ ያሉ ልጆች አሉ ። እንደነ ያሬድ ፤ ወገኔ ፣ አለምብርሐን ፣ ብርሀኑ አይነት ተጫዋቾች አሉ ። ስለዚህ እነዚህን ወጣቶች ሰብስበን በድግምግሞሽ ስራ ብሔራዊ ቡድንን መተካት ይኖርብናል ። ቢያንስ ከዚህ በአንድ ጊዜ ስድስት አልያም ሰባት ተጫዋቾች ብናመጣ እንኳን በጣም ጥሩ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው ።