“በዛሬው ድላችንና ለክለቤ የመጀመሪያ የሆነችውን ግብ ስላስቆጠርኩ በጣም ተደስቻለሁ”
“በተፈጥሮዬ የጌም ተጨዋች ነኝ፤ በቅ/ጊዮርጊስ ቆይታዬም ልምምድ ላይ ግድየለሽ ተጨዋች ነው ተብሎ የሚነገረው ነገር የእውነት ነው”
አቤል እንዳለ /ቅ/ጊዮርጊስ/
ቅ/ጊዮርጊስ ወደ ባህርዳር በተጓዘበት የቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታው አዳማ ከተማን 4-2 በማሸነፍ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ ከሚቀረው ከመሪው ፋሲል ከነማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ 4 ሊያጠብ ችሏል።
የቅ/ጊዮርጊስ ክለብ በዛሬው ፍልሚያ ባለድል ሲሆን ለክለቡ የተቆጠሩትን ግቦች አቤል እንዳለ ሁለቱን ደግሞ አማኑኤል ገብረ ሚካሄል እና የቡድኑ ካፒቴን ጌታነህ ከበደ ያስቆጠሩ ሲሆን ከእነዚህ ግቦች ውስጥ አቤል እና አማኑኤል ያገቡትም ግብ በቡድኑ ታሪክ የመጀመሪያ ሆኖም ተመዝግቦላቸዋል።
ቅ/ጊዮርጊስ በዕለቱ ተጋጣሚውን ባሸነፈበት ጨዋታ 3-0 እስኪመራ ድረስ ከተጋጣሚው በእንቅስቃሴ ተሽሎ ቢገኝም ሁለት ጎሎችን ካስተናገደ በኋላ ደግሞ መቀዛቀዝ ታይቶበታል።
ቅ/ጊዮርጊስ በዛሬው ጨዋታ ተጋጣሚውን ድል ካደረገ በኋላ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ ገብቶ ጥሩ እንቅስቃሴን ካሳዩት ተጨዋቾች መካከል አንዱ የሆነውን እና በኋላም ላይ በነበረው የጨዋታ ሪትም ያልቀጠለውን አቤል እንዳለን በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ የሀትሪክ ስፖርቱ ድረ ገፅ ጋዜጠኛ መሸሻ ወልዴ አናግሮት ምላሽ ሰጥቶታል።
- ማሰታውቂያ -
ሀትሪክ፦ አዳማ ከተማን ረታችሁ፤ ወደ አሸናፊነት መንፈሱም ተመለሳችሁ። ጨዋታው ምን መልክ ነበረው?
አቤል፦ በቅድሚያ ከውጤት ማጣት ጋር በተያያዘ ቡድናችን ላይ ተፈጥሮብን በነበረው ጫና ምክንያት የዛሬውን ግጥሚያ በአሸናፊነት በመወጣታችን በጣም ደስ ብሎኛል። ወደ ጨዋታው ሳመራ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድናችን በዛሬው ጨዋታ ውጤቱ በጣም ያስፈልገው ስለነበር ጥሩ ተነሳሽነት ነበረው። ወደ እነሱ የግብ ክልል እንቃረብም ነበር። በዛ መነሻነትም ሁለት ግብ አስቆጠርን። በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ግን ሶስተኛውን ግብ ካስቆጠርን በኋላ ሌላ ተጨማሪ ግቦችን ማስቆጠር ሲገባን አስቀድሞ መቀዛቀዝ ስላሳየንና ቸልተኛ እየሆንም ስለመጣን ሁለት ግቦችን በማስተናገድ ራሳችን ላይ መጨናነቅን ፈጥረናል። በመጨረሻም አራተኛ ግብ ማስቆጠራችን ሊያረጋጋንም ችሏል”።
ሀትሪክ፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ከተቀላቀልክ ጀምሮ የመጀመሪያ ግብህን ነው ያስቆጠርከው ምን ስሜት ተፈጠረብህ? ከአብስራ ጋር የገለፅከውስ የደስታ አገላለፅ…
አቤል፦ ለቅ/ጊዮርጊስ በስሜ የተመዘገበችውን የመጀመሪያዬን ግብ በማስቆጠሬ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ይህች ግብም ቡድናችን በውጤት ማጣት ውጥረት ውስጥ ባለበት ሰዓት ያስመዘገብኳት ስለሆነች ጭምርም ነው የደስታዬን ስሜት ልዩ ሊያደርገው የቻለው።
ግቧን ካስቆጠርኩ በኋላ ከአብስራ ጋርም በደንብ ተቃቅፈን ልድሰት የቻልኩት እሱ እንደ ወንድሜ የማየው እና የምወደው ጓደኛዬ ስለሆነ ነው።
ሀትሪክ፦ 3ለ0 መራቹና 2 ተከታታይ ግቦች ተቆጠረባችሁ፤ ያን ጊዜ ስሜታችሁ ምን ይመስል ነበር። እንዴትስ ነው ግቦቹን ያስተናገዳችሁት?
አቤል፦ አዳማዎች ተከታታይ ግቦችን በእኛ መዘናጋት ባስቆጠሩብን ጊዜ የእውነት ነገሮችን ከባድ እያደረገብን ነበር። ግቦቹም የተቆጠሩት ከሁለት ሙከራ ሁለቱም ነበሩ። ያም ሆኖ ግን ሰዓቱ እየገፋ በመጣበት ሰዓት አራተኛዋን ግብ ማስቆጠራችን እፎይታን ሰጥቶናል።
ሀትሪክ፦ አዳማ ከተማን በጨዋታው እንዴት አገኘሃቸው?
አቤል፦ አልዋሽም ፈትነውናል። እነሱ ብቻ ሳይሆኑ የእኛ ሁሉም ተጋጣሚ ቡድኖች ከኛ ጋር ሲጫወቱ ጠንክረው ነው የሚመጡት። ለቅ/ጊዮርጊስ የሚተኛም የለም።
ሀትሪክ፦ በኳስ ችሎታህ ጥሩ ብቃት እንዳለህ ብዙዎች መስክረውልካል፤ ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚነት ከመሰለፍ እና ካለመሰለፍ ጋር በተያያዘ ግን በአንተ ዙሪያ ከዓምና ጀምሮ ብዙ ነገሮች ሲባሉ ከርመዋል። ለእዚህ ምላሽ ባለቤቱና ትክክለኛው ሰው አንተ ስለሆንክ በጉዳዩ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቤል፦ ወደ ቅ/ጊዮርጊስ ካመራሁበት ጊዜ ጀምሮ ለእዚህ ቡድን ብዙ የስኬት ስራዎችን የመስራት ፍላጎቴ በጣም ከፍተኛ ቢሆንም እኔ በተፈጥሮዬ የጌም ተጨዋች ነኝ፤ በልምምድ ሜዳ ላይ ደግሞ ግዴየለሽ የሆንኩ ተጨዋች ነኝ። እንዲህ ሆኜ ሳለው ግን በልምምድ ሰዓት ላይ ያሾፋል ይቀልዳል ይፈራልም የሚለው ነገር እኔን የሚያስማማኝ አልነበረም። እኔን የሚያስማማኝ ልምምድን በአግባቡ ጠንከር አድርጎ አይሰራም የሚለው እና በእኔ ዙሪያም ሰዎች አቤል ልምምድ ላይ ግዴለሽ ነው ብለው የሚገልፁኝ ነገር ትክክል ናቸው። ይህን ክፍተቴንም እያረምኩ እና በልምምድ ላይም ጠንክሬ እየሰራው በመምጣት በቀጣይነት የቡድኑ ቁልፍ ተጨዋች ለመሆን ከፍተኛ ጥረትን አደርጋለሁ።
ሀትሪክ፦ ለቅ/ጊዮርጊስ በቋሚ ተሰላፊነት ለመጫወት የቻልከው በቡድናችሁ ዙሪያ ሰሞኑን በነበራችሁ ውይይት መሰለፍ የሚገባቸው ልጆች ይግቡ በሚለው ነው? ወይንስ በሌላ?
አቤል፦ በዛሬው ጨዋታ ለክለቤ በቋሚ ተሰላፊነት ልጫወት የቻልኩት ሰሞኑን በነበረን ውይይት መግባት አለበት ተብዬ ሳይሆን ለቡድኑ የማልሰለፍበት ምክንያት እና ችግሬ በአሰልጣኞቼ ስለተነገረኝ እና በክፍተቴም ዙሪያ ልምምድ ላይ በደንብ ሰርቼ ስለመጣው ነው።
ሀትሪክ፦ ጎል ያስቆጠርክበት መንገድ በብዙዎች ዘንድ አድናቆት እንዲያሰጥህ አድርጓል፤ በእዚህ ዙሪያ የምትለው ነገር ካለ?
አቤል፦ ኳሷን እንዳገኘሁ እና ጥፋት እንደተፈፀመብኝ ለመመደቅ አስቤ ነበር። ወዲያው ግን የተከላካይ ስፍራ ተጨዋቾቹ እና የግብ ጠባቂውን አቋቋም ሳይ ቦታቸውን እንደከፈቱት ስለተረዳው ጥሩ የሚባለውን ግብ አስቆጠርኩኝ። በግቧም በጣም ተደሰትኩኝ።
ሀትሪክ፦ የሁለተኛው አጋማሽ ላይ በእንቅስቃሴህ አንተም ቀዝቀዝ ያልክበት ሁኔታ ተፈጥሯል?
አቤል፦ የእውነት ነው። መጀመሪያ ላይ እንደነበረኝ አይነት አይደለም ስጫወት የነበርኩት። ተቀዛቅዤ ነበር። ይሄ የሆነውም በብሽሽቴ አካባቢ የህመም ስሜት ስለተሰማኝም ነው።
ሀትሪክ፦ የቅ/ጊዮርጊስ የዛሬው ድል ቀጣይነት ይኖረዋል?
አቤል፦ አዎን፤ ያለዚያማ ለምን እናሸንፋለን። አሁን ቡድናችን ወደ አሸናፊነቱ መንፈስ ተመልሷል ይሄ ድልም ይቀጥላል።
ሀትሪክ፦ በቤት ኪንግ ፕሪምየር ሊጉ ፋሲል ከነማ ሊጉን እየመራ ይገኛል። ሻምፒዮና የመሆን ተስፋችሁ የቱን ያህል ነው?
አቤል፦ አሁን እኛ ስለ ራሳችን ቡድን እያንዳንዱ ጨዋታ እንጂ የምናስበው ሊጉን ስለሚመራው ቡድን ፋሲል አይደለም። የራሳችንን ስራ ከሰራን እና እያንዳንዱን ግጥሚያ ማሸነፍ ከቻልን ውድድሩ ገና ከመሆኑ አንፃር ሻምፒዮና የማንሆንበት ምክንያት የለም።
ሀትሪክ፦ የኢትዮጵያ ቡናው ዊሊያም ሰለሞን አቤል እንዳለ ለእኔ እግር ኳስ ተጨዋችነች ባለውለታዬ የሆነ ተጨዋች ነው ብሎሃል። በእዚህ ዙሪያ ምን ትላለህ?
አቤል፦ ዊሊያም በጣም ጎበዝ እና ጥሩ አቅም ያለው ተጨዋች ነው። ሁለታችንም የሀረር ልጆች ስለሆንንም በደንብም ነው የምንተዋወቀው። ሲጫወት ካየሁበት ጊዜ ጀምሮ ጥሩ ደረጃ ላይ እንዲደርስ እና ወደ ክለብ ደረጃም በመሸጋገር ወጥቶ እንዲጫወት ስለምፈልግ ጠንክሮ መስራት እንዳለበትም እመክረዋለሁ እና አሁን በሚገኝበት ደረጃ በጣም ደስተኛ ነኝ።
ሀትሪክ፦ በመጨረሻ….?
አቤል፦ ቅ/ጊዮርጊስ ጎሎችን ካስቆጠረ በኋላ የሚዘናጋውን ነገር ማሻሻል አለበች ይሄ ችግር አምና ታይቶበታል። ይሄን ማረም ከቻለ የአሸናፊነትን መንፈስ ማስቀጠል የሚያስችል አቅሙ ስላለው ዘንድሮ ጥሩ ውጤት ያመጣል።