ባህርዳር ከተማ ጠንካራ ፍልሚያ በማድረግ ከ2014ቱ 12ኛ ደረጃ ዘንድሮ ከፍተኛ ለውጥ በማምጣት ከመልካም ጨዋታ ጋር በአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው እየተመራ 2ኛ ደረጃ በመያዝ ለኮንፌዴሬሽን ካፕ ሀገር የመወከል እድል አግኝቷል። መላው ደጋፊዎቹን ያስጨፈረው ውጤትን ተንተርሶ አሰልጣኙ ትልቅ ሙገሳ እየቀረበለት ነው….የሀትሪክ ድረገጹ ባልደረባ ጋዜጠኛ ዮሴፍ ከፈለኝ ደግሞ ውጤታማ መሆኑን ተከትሎ የዋሊያዎቹ ሁለተኛ ሰው የመሆን እድል ያገኘውን አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛውን አነጋግሮታል….
ሀትሪክ:- ለኮንፌዴሬሽን ካፕ ያለፋችሁበት የአመቱ ጉዞ ምን ይመስላል..?
ደግአረገ:- ከባድ የውድድር ጊዜ ነው ያሳለፍነው… ያም ሆኖ አመቱን በጥሩ ውጤት ነው ያሳለፍነው በዚህም ደስተኛ ነኝ ያሳካነው ውጤትም ትልቅ ትርጉም አለው የባህርዳር ከተማ የዚህን አመት ስኬት ለመዘርዘር ያህል ሁለተኛ ሆነን በማጠናቀቃችን በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ካፕ ተሳታፊ መሆናችንን አረጋግጠናል ከ8 ያላነሱ ተጨዋቾችን ለብሄራዊ ቡድን አስመርጠናል ሶስት ተጨዋቾቻችን ለአመቱ ኮከብነት እጩ ሆነዋል ሱፐር ስፖርት በመረጠው የአመቱ ምርጥ 11 ውስጥም ሶስት ተጨዋቾችን አስመርጠናል በአጠቃላይ ምርጥ ጊዜ አሳልፈናል እንደ ቡድንም እንደ ግልም ለውጥ ያመጣንበት አመት ነው ወደፊት የሚቀረን ስራ ቢኖርም ተመልካቹን የሚያዝናና ቡድን ገንብተናል ብዬ አምናለሁ ለባህርዳር ከተማ ደጋፊና ቤተሰብ ደስታ ፈጥረናል የሚል እምነቱ አለኝ።
ሀትሪክ:- በኮንፌዴሬሽን ካፑ ቅድመ ማጣሪያ ተጋጣሚያችሁ አዛም ሆኗል…ምን ትላለህ..?
- ማሰታውቂያ -
ደግአረገ:- አዛም የተደራጀ ቡድን ነው ዝግጅቱንም ቀድሞ ነው የጀመረው ያም ቢሆን እኛም ጠንካራውን ባህርዳር ይዘን የምንቀርብ ይሆናል ተገቢውን ትኩረት ሰጥተን እንዘጋጃለን የዝውውር መስኮት በመከፈቱ ውል የጨረሱትን አሳምኖ የማስፈረም አዳዲስ መጨመር በሚለቁ ምትክ ቦታው ላይ መተካት የቤት ስራችን ሆኗል በርግጥ ጥረታችን ገና አልተቋጨም እስካሁን ዝግጅት ያልጀመርነው በዚህ ምክንያት ነው ነገር ግን ባለችን አጭር ጊዜ ተዘጋጅተን እንቀርባለን እንደ መልካም አጋጣሚ የመጀመሪያ ጨዋታ በሜዳችን የማድረግ እድሉ ይፈጠራል ባህርዳር ስታዲየም እንዲደረግ ክልሉም ሆነ ከተማው ጥረት እያደረጉ በመሆኑ ትልቅ ተስፋ አሳድሮብናል …
ሀትሪክ:- ደጋፊውን እንዴት አገኘኸው …?
ደግአረገ:- የቡድናችን ደጋፊዎች የሚገርሙ ደጋፊዎች ናቸው ቡድናችን በደጋፊው የሚገርም ድጋፍ ያልተለየው ቡድኑን እንደ ጉዳዩ የሚያይ ደጋፊ ባለቤት በመሆናችን የዚህ ቡድን አሰልጣኝኝ በመሆኔም እኮራለሁ በተመዘገበውም ውጤት እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ቡድናችን ከከተማው አልፎ በመላው አገሪቱ የሚወደድና ደጋፊም ያለው መሆኑ ያስደስታል። የነበረው የደጋፊው ደስታ አቀባበሉ ላይ ያየነው ፍጹም ከጠበቅነው በላይ እጅግ ስሜት የሚነካ በመሆኑ ማመስገን እፈልጋለሁ። በባህርዳር ስታዲየም መካሄድ አለበት ብለን የምንሯሯጠውም ለዚህ ነው… እናንተን በማስደሰቴ ደስ ብሎኛል በቀጣይም በተሻለ ውጤት እንደምናስደስታችሁ ተስፋ አለኝ ውጤቱም ለደጋፊው ይገባዋል ብዬ አምናለሁ በኮንፌዴሬሽን ካፕ ጠንካራ ተጋጣሚ ቢገጥመንም ከእናንተ ጋር ትንሽ ርቀት እንጓዛለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ ከእግዚአብሄር ጋር ይሳካል ብዬም አምናለሁ ለደጋፊው ከዚህ በላይ ይገባዋል ለደጋፊዎቹ፣ የአቀባበል ስነስርዓቱን ላዘጋጁ የክለቡ አመራሮች የደጋፊው ማህበርና አመራሮች ለከተማው ከንቲባና የክለቡ የበላይ ጠባቂ ያለኝን ምስጋና መግለጽ እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ:- ወደ ኋላ መለስ ብለህ ሰላሳ የሊጉን ጨዋታዎች ስትመለከት ዋንጫ ያጣችሁት በየትኛው ጨዋታ ይመስልሃል…?
ደግአረገ:- እንደ እግርኳስ ሜዳ ላይ የሚከሰቱ ነገሮች ይከሰታሉ አታቆማቸውም.. ምናልባት ግን ዋንጫ ያጣነው በተጨዋቾቼ የልምድ አለመኖር ይመስለኛል በተጨዋቾቼ ላይ የነበረው ጉጉት በተለይ ደግሞ ጊዮርጊስ ነጥብ ጥሎ በቀጣይ በነበረን ጨዋታ ላይ አሸንፎ ደጋፊውን ለማስደሰት የነበረው ጉጉት ዋጋ አስከፍሎናል ጫና መቋቋም አለመቻላችን ይመስለኛል ይሄ ደግሞ ከልምድ ጋር የተያያዘ ነው በተቃራኒው ጊዮርጊስ በልምድ የካበተ ክለብ ነው ዋንጫ በተደጋጋሚ ያነሳ ትልቅ ስም የገነባ ትልቅ ታሪክ ያለው ነውና ያ ልዩነት ዋጫውን እንዳሳጣን ይሰማኛል።
ሀትሪክ:- እንደ ጨዋታስ ከዋንጫ ወደ ኋላ ያስቀራችሁ…?
ደግአረገ:- ለዋንጫ ማጣታችን ትልቅ ምክንያት የምለው ከራሱ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታ ነጥብ መጣላችን ነው። ማሸነፍ የምንችልበት አጋጣሚ ተፈጥሮ አለመጠቀማችን የነበረን ጥሩ የነበረ አቋምን በውጤት አለማጀባችን ከመመራት ተነስተን መምራት ችለንም ማስጠበቅ አለመቻላችን ጎድቶናል ብዬ አምናለሁ ያ ጨዋታ ትልቅ ትርጉም ነበረው ከሀድያ ሆሳዕና ጋር በጨቀየ ሜዳ ላይ መጫወታችን ሀድያዎች ተጠቅመው ነጥብ መጣላችንም እንደ ምክንያት ይነሳል።
ሀትሪክ:- በሲዳማ ቡና 4 ለ 0 የተሸነፋችሁበትስ ጨዋታ…?
ደግአረገ:- ዋንጫውን የሚወስነው ጊዮርጊስ በራሱ እጅ ስለነበር ብዙም ተስፋ አልነበረውም የተጨዋቾቼ ስሜትም ያ ይመስለኛል እነሱ ነጥብ ካልጣሉ ዋጋ የለውም ነበረና የተዘናጋን ይመስለኛል የሆነው ሆኖ ግን ጊዮርጊስን ጫና ላይ ለመክተት አሸንፈን መውጣት ይጠበቅብን ነበር በቀጣይ የምንሰራበትና የሚስተካከል ይሆናል እንደ አጠቃላይ ከልክ ያለፈ ጉጉትና ያን ጉጉት መቆጣጠር አለመቻላችን ጎድቶናል ብዬ አምናለሁ
ሀትሪክ:- የዋሊያዎቹ ም/ል አሰልጣኝ ሆነህ እየሰራህ ነው…የባህርዳር ከተማ ስኬቴ አስመርጦኛል ማለት ትችላለህ…?
ደግአረገ:- ይመስለኛል… በዚህ አጋጣሚ ረዳቶቼን በጣም አመሰግናለሁ… ትልቅ ስራ ሰርተናል በወጣት የተገነባ ሃላፊነቱን በሚገባ የተወጣ የአሰልጣኞች ስብስብ የጋራ ውጤት ያመጣው ድል ነው… የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተመዘገበው ውጤት ጠንካራ አቋማችን ወጥ መሆኑ ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑ ይህን እድል ፈጥሯል ብዬ እገምታለሁ።
ሀትሪክ:- ዋሊያዎቹ በአሜሪካ የሚያደርጉት ጨዋታ ለግብጹ ፍልሚያ የሚሰጠው ጥቅም በምን መልኩ ይገለጻል…?
ደግአረገ:- ጥሩ የሚባል ጥቅም ይኖረዋል ብዬ አምናለሁ….. ነገር ከብሄራዊ ቡድኑ ጋር ተያይዞ ዋና አሰልጣኙ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማሪያምን መጠየቁ ይሻላል ብዬ አስባለሁ በቀጣይ በሚሰጥ መግለጫ ላይም ምላሹ ሰፋ ብሎ ይሰጣል ብዬ አምናለሁና ጥያቄው ቢዘለኝ…?
/ ቃለምልልሱን የሰራነው ረቡዕ ዕለት ነው/
ሀትሪክ:- ዋሊያዎቹን የማሰልጠኑን እድል ማግኘት የፈጠረብህ ስሜት ምን ይመስላል…?
ደግአረገ:- የማንም አሰልጣኝ ህልም የሆነውን ሀገርን የማገልገል እድል ሲሰጠኝ ተደስቻለሁ ኩራትም ተሰምኛል… በርግጥ በዚህ ሰአት የብሄራዊ ቡድን ሃላፊነቱን አገኛለሁ ብዬ ባልጠብቅም የባህርዳር ከተማ ስኬቴ እንዳስመረጠኝ አምናለሁ ጠንክሬ ሰርቼ አገሬን በበለጠ እንደማገለግል ተስፋ አደርጋለሁ በነገራችን ላይ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን ሲያመጣ ከባህርዳር ከተማ ስራዬ ጋር እንዳይጋጭ አድርጎ ስለነበርና ብሄራዊ ቡድኑን እንዳግዝ የሚጠይቅ ስለነበር ከክለቤ ጋር ተስማምቼ እየሰራሁ ነው።
ሀትሪክ:-ከዋሊያዎቹ ጋር በነበረህ ቆይታ ያገኘኸው ልምድ አለ…?
ደግአረገ:- ከዋሊያዎቹ ጋር ያደረኩት የመጀመሪያ ጉዞ ወደ ሞዛምፒክ ሄደን ማላዊ ጋር አቻ የተለያየንበት ጨዋታ ነው ጥሩ ልምድ ይዤ ተመልሻለሁ ብዬ አምናለሁ በኮንፌዴሬሽን ካፑም ለሚኖረኝ የኢንተርናሽናል ውድድር ጉዞ የተወሰነ እውቀት አግኝቻለሁ። በዚህ አጋጣሚ አገሬን እንዳገለግል እድሉን የሰጠኝን ፌዴሬሸኑን ማመስገን እፈልጋለሁ።
ሀትሪክ:- የመጨረሻ የምትለው ቃል ካለህ…?
ደግአረገ:- ለባህርዳር ከተማ የቦርድ አመራሮች፣ ለደጋፊው ለማህበራቸውና አመራሮቹ ፣ በአጠቃላይ በክለቡ ዙሪያ ሃላፊነት ወስደው ለሚሰሩ ሰዎች ስራዬን በነጻነት እንድሰራ ምቹ ሁኔታን ስለፈጠሩልኝ በጣም አመሰግናለሁ… ወደር የማይገኝላቸው በሄድንበበት ሁሉ የማይጠፉ ህይወታቸውን ሁሉ ለአደጋ እያጋለጡ ከጎናችን ለሆኑ ደጋፊዎች ምስጋናዬ ይድረሳቸው እንዲሁም የበላይ ዘለቀ አስጨፋሪዎችን አመሰግናለሁ የከተማው ነዋሪዎች እናቶችና አባቶች በየእምነቱ እየሄዱና እየጸለዩ ከጎናችን ነበሩና እነሱንም አመሰግናለሁ ። ረዳቶቼ በቅንነትና በታዛዥነት ከጎኔ ሆነው ከራሳቸው አልፈው የሌላውን በመሸፈን ትልቅ እገዛ አድርገው ስራው ቀለል እንዲለኝ አድርገዋልና በጣም ነው የማመሰግናቸው… ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱና ኢንስትራክተር ሰውነት ቢሻው ሙያዊ እገዛ አድርገውልኛልና አመሰግናለሁ። ውዷ ባለቤቴ ናርዶስ ጽጌ ስራዬን በነጻነት እንድሰራ አዕምሮዬ ወደ ቤት እንዳይሄድ ልጆቼ ሚስቴ ብዬ እንዳልጨነቅ ሙሉ ሃላፌነት በመውሰድ በውጤት ከፍታና ዝቅታ ከጎኔ በመሆን ትልቅ እገዛ አድርጋልኛለችና ከልብ እንደምወዳት እንደማከብራት መግለጽ እፈልጋለሁ ኳሱን በመከታተል ከኔ ጋር የሚጨነቁትን ቤተሰቦቼንም አመሰግናለሁ በተረፈ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች እግርኳሱ ጎልቶ እንዲወጣ በተለይ ደግሞ ቡድናችን እያስመዘገበ የነበረውን ውጠለት ማራኪ አጨዋወት ለህዝብ ተደራሽ በማድረግ ላበረከቱት አስተዋጽዎ አመሰግናለሁ ለአንተና ለሀትሪክ ድረገጽም ያለኝ ክብር ትልቅ ነው ሀሳቤን እንድገልጽ ለሰጣችሁኝ እድል አመሰግናለሁ።
ሀትሪክ:- እኛም እናመሰግናለን …