የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ የካቲት 25 2016 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
በሳምንቱ መርሃግብር በተደረጉ ጨዋታዎች ሰባቱ በመሸናነፍ ቀሪ አንዱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ 22 ጎሎች ተቆጥረዋል ፥ ከግቦቹ 1 በፍፁም ቅጣት ምት እና 2 በራስ ላይ የተቆጠሩ ናቸው። 44 ቢጫ ካርድ ለተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ሲሰጥ የተመዘገበ ቀይ ካርድ የለም ።
በተጫዋቾችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፈ ውሳኔ አዲስ ተስፋዬ(ኢትዮጵያ መድን) እና አብነት ደምሴ(ወላይታ ድቻ) የተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቀቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት አንድ ጨዋታ እንዲታገዱና የገንዘብ ቅጣት 1500 ብር እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በክለቦች የሃዋሳ ከተማ ስድስት ተጫዋች አብዱልባሲጥ ከማል ፣ በረከት ሳሙኤል፣ ቸርነት አውሽ፣ አቤኔዘር ዬሀንስ፣ ፀጋአብ ዬሀንስ እና ተባረክ ሄፋሞ ፤ የፋሲል ከነማ አምስት ተጫዋቾች አምሳሉ ጥላሁን፣ እዬብ ማትያስ፣ ዬናታን ፍስሀ፣ ምኞት ደበበ እና ቃልኪዳን ዘላለም እንዲሁም የአዳማ ከተማ አምስት ተጫዋቾች ሱራፌል አወል፣ ቻርልስ ሪባኑ፣ ፍቅሩ አለማየሁ፣ ዬሴፍ ታረቀኝ እና ሙሴ ኪሮስ በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ሶስቱ ክለቦች እያንዳንዳቸው የገንዘብ ቅጣት ብር 5000/አምስት ሺ/ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡