ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2015 25ኛ ሳምንት በሃዋሳ ከተማ ሃዋሳ ዩንቨርሲቲ ስታዲየም በተደረጉ ጨዋታዎች አራት ጨዋታዎች በመሸናነፍ ቀሪ አራቱ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቁ 20 ጎሎች በ17 ተጫዋቾች ተቆጥረዋል። የጎሎቹ አገባብም 17 በጨዋታ ሶስት በፍፁም ቅጣት ምት ነው። በሳምንቱ 41 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ ሲገሰፁ አንድ ተጫዋች በሁለተኛ ቢጫ ቀይ ካርድ ተመልክቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ረቡዕ ግንቦት 16 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያ(ዎች)ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ የተለያዩ ውሳኔዎችን አስተላልፏል።
በተጫዋችና ቡድን አመራሮች ደረጃ በተላለፉ ውሳኔዎች 5 ተጫዋቾች ላይ ቅጣት ተላልፏል። ያሬድ ዳዊት(ወላይታ ድቻ) ሁለተኛ ቢጫ ካርድ የሚያስጥ ጥፋት በመፈፀሙ ቀይ ካርድ አይቶ ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ለፈፀመው ጥፋት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገድ፥ ኤሪክ ካፓይቶ(አርባምንጭ ከተማ)፣ ፍሪምፖንግ ሜንሱ(ቅዱስ ጊዮርጊስ)፣ ረመዳን የሱፍ(ቅዱስ ጊዮርጊስ) እና ዮሴፍ ዮሀንስ(ድሬደዋ ከተማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ በመመልከታቸው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በክለቦች ደረጃ በታዩ ሪፖርቶችም በአራት ክለቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈዋል። ድሬደዋ ከተማ እና ለገጣፎ ለገዳዲ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ከአራት በላይ ተጫዋቾች በተለያዩ ጥፋቶች ካርድ የተሰጣቸው በመሆኑ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ክለቦቹ የገንዘብ ቅጣት ብር 5000 /አምስት ሺ/ እንዲከፍሉ ፥ አርባ ምንጭ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የራሳቸውን ቡድን የክለብና የቡድን አመራሮች አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር
50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
ወላይታ ድቻ ክለቡ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የዕለቱን ጨዋታ አመራሮችን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት ሲሆን ከዚህ በፊትም የክለቡ ደጋፊዎቹ አፀያፊ ስደብ በመሳደብ ከተቀጡት ቅጣት ሊታረሙ ባለመቻላቸው ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት ብር 75000/ሰባ አምስት ሺህ / እንዲከፍል ተወስኗል፥ ከዚህም በተጨማሪ የክለቡ ደጋፊዎች ከስታድየም ቅጥር ግቢ ውጭ የፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ንብረት በሆነው ተሽከርካሪ ላይ ድንጋይ በመወርወር ጉዳት ስለማድረሳቸው ሪፖርት በመቅረቡ ክለቡ የተጎዳውን ተሽከርካሪ እንዲያሰራ ወይም ባለንብረቱ አስልቶ በሚያቀርበውን ዋጋ መሰረት ክፍያ እንዲፈፅም ወስኗል ።