“ሁለት የቡድኑ አባላት አልተመለሱም ጠፍተዋል በዚህም እንደ ፌዴሬሽን አዝነናል”
አቶ ባህሩ ጥላሁን
/ የፌዴ.ዋና ስራ አስፈጻሚ/
” በሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታ ለግብጹ ፍልሚያ ግብአትና የተጨዋቾቻችንን በራስ መተማመን ለማሳደግ ተጠቅመንበታል”
ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማሪያም
/የዋሊየዎቹ ዋና አሰልጣኝ/
” ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አላት? ሱራፌል የኢትዮጵያ ተጨዋች ነው ወይ ? ብለው ጠየቁን”
አቶ ዳዊት አርጋው
/ኤጀንትና የጉዞው አስተባባሪ/
- ማሰታውቂያ -
በዋሊያዎቹ የአሜሪካ ጉዞ “የኢትዮጵያ ተጨዋቾች ዕይታ ውስጥ የገቡበትን መልካም አጋጣሚ አግኝተናል የትውልደ ኢትዮጵያዊያን አቅምም ያየንበት ነው ” ሲሉ የዋሊያዎቹ አሰልጣኝ ኢንስትራክተር ዳንኤል ገ/ማሪያም ተናገሩ።
ስለ አሜሪካ የብሄራዊ ቡድኑ ጉዞ በፈዴሬሽኑ ጽ/ቤት በተሰጠው መግለጫ ላይ አሰልጣኙ እንዳሉት “በኢትዮጵያና ጋያና ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኞች መሃል የሙያ ሽግግርና ምክክር አድርገናል እኔም ተምሬበታለሁ ተጨዋቾቻችንም ያለባቸውን የግብ የማስቆጠር ችግር በተወሰነ መልኩ ተቀርፎ ያየንበት አጋጣሚ ነው ” ሲሉ ተናግረዋል። ኢንስትራክተር ዳንኤል እንደገለጹት “ሁለቱን ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ተጨዋቾች ተጠቅመናል በግራ መስመር የሚጫወተው ማርከስ ፍጹም ዲሲፕሊንድና ከ80-90 በመቶ ምርጥ ነበር ግብ ጠባቂው ይለያል እኔ ራሴ ተገርሜበታለሁ የፍጹም ቅጣት ምት ሲሰጥብን ግብ ጠባቂው ይመልሰዋል እናንተ ተረጋጉና ኳሱን አውጡ ብያቸው በረኛው መልሶታል በዚሁ አጋጣሚ ሁለቱንም ተጨዋቾች ጨምሮ ሌሎች ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዋሊያዎቹን እንዲያገለግሉ ፌደሬሽኑ ከሚመለከተው አካል ጋር የሚነጋገርበት ይሆናል እንደ ቡድን በሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታ ለግብጹ ፍልሚያ ግብአትና የተጨዋቾቻችንን በራስ መተማመን ለማሳደግ ተጠቅመንበታል” ሲሉ አስረድተዋል።
የፌዴሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ባህሩ ጥላሁን በበኩላቸው ጉዞው በመሳካቱ እንደሚኮሩ ተናግረዋል።
“በአንድ ሚዲያ ላይ ጉዞው እንደማይሳካ ሲነገር የነበረው ጉዞ ተሳክቶ ስለመጣው ደረቴን ነፍቼ የምሰጠው መግለጫ ነው” ያሉት አቶ ባህሩ ” ተጨዋቾቻችን የመታየት እድል እንዲያገኙ አድርገናል በሁለቱ ጨዋታ ሽመልስ በቀለ፣ ቢኒያም በላይ ፣ አቤል ያለው፣ማርከስ
ጋቶች ፓኖም፣ ረመዳን የሱፍና ሱራፌል ዳኛቸው የመታየት እድል አግኝተዋል አቤል ውል ስላለው ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር እንዲነጋገሩ ነግረናቸዋል ጋቶች ግን ከውል ውጪ ስለሆነ በቅድሚያ ዕድሉን የሚሞክር ይሆናል” ሲሉም አብራርተዋል።
በዚሁ መግለጫ ላይ ከፍተኛ ትኩረት የሳበው የኡመድ ኡኩሪ ጉዳይ ነው። ኡመድ ለአሜሪካ ጉዞ ቲኬት ራስህን ቻል ተብያለሁ በዚህ ምክንያት ራሴን ከብሄራዊ ቡድን አግልያለሁ ማለቱ ዋና ስራ አስፈጻሚውና አሰልጣኙን አበሳጭቷል። አቶ ባህሩ በሰጡት ምላሽ ” ከኡመድ ኡኩሪ ጋር በተያያዘ ጥያቄው መሆን ያለበት ዑመድ ለምን ተመረጠ ነው ወይስ ለምን መሄድ አለበት ? አሁን ባለበት ሁኔታ ዑመድ ለብሔራዊ ቡድን ይመጥናል ወይ ለሚለው ምላሹን ለእናንተ ልተወው ፌዴሬሽኑ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድጋፍ እንዲያደርግልን በላከው የመጀመርያው ስም ዝርዝር ኡመድን ጨምሮ የአሰልጣኝ አባላት እና የተወሰኑ ተጫዋቾች ስም አልተላከም። በሁለተኛ ደብዳቤ ደግሞ አሰልጣኞቹ ኡመድን ጨምሮ የሚሄዱትን ስም ዝርዝር ስንልክ የሱ ስም በ42ኛ
ላይ ተፅፏል። ፌዴሬሽኑ ቀጠሮ የማፍጠን ስልጣን ስሌለው ቀጠሮ አሳጥሮ እንዲገባ ተነገረው ነገር ግን አልሆነም በዚህ ሁኔታ እያለንም ኢንስትራክተር ዳንኤል ኡመድ ምን ሊሰራልኝ ነው የጠራችሁት ? ወቅታዊ አቋሙን እኔ አይቼው አላውቅም በየትኛው መንገድ ነው የተጠራው ? እያሉ እየተቃወሙም አሰልጣኙን ተጭነው ቡድኑ ውስጥ እንደተካተተ የነበረውን በማለት ሂደት አብራርተዋል።
“ክፍያህን ራስህ ቻል መቼ አልነው? ማነው የተናገረው?
ክፈል የተባለው ክፍያ የቱ ነው ? ኤምባሲ ከተገባ በኋላ የአስቸኳይ ሲሆን ቢጫው ይሰጣል እርሱ ግን ነጩን ተቀበለ። አሰልጣኙም ሌሎች ተጫዋቾች ነጩን ነበር የተቀበሉት ግን ሄደው አስተካከሉት የእርሱ ግን ባለመስተካከሉና ነጭ በመሆኑ ቪዛውን የሚቀበልበት ቀን ሰኞ ሆነ እኛ ግን እሱንም አካተን 11 ቁጥር ማልያ አዘጋጅተን ምን ብለን ነው የምናስቀረው ? “ሲሉ የጠየቁት ያመ አቶ ባህሩ “ራሴን ከብሔራዊ ቡድን አግልያለው የሚለውን አንቀበልም ለብሔራዊ ቡድን ላበረከታቸው
አስተዋጽዎም ክብር አለን። በአሜሪካ ጉዞ ባነሳው ቅሬታ ግን ተጠያቂ አንሆንም በአጠቃላይ ራሱን ከብሔራዊ ቡድን ለማግለል ፌዴሬሽኑን ምክንያት ማድረግ ተገቢ አይደለም ስለ ኡመድ ኡኩሪ በዚህ ደረጃ መከራከርም
የለብንም የቀረው ሊዮኔል ሜሲ ነው እንዴ..?” ሲሉ በሰላ ሂስ ተችተዋል።
ከሁለቱ የወዳጅነት ጨዋታዎች በመጀመሪያው ጨዋታ 260 ሺ ዶላር መገኘቱን ያብራሩት አቶ ባህሩ ወደ 1000 ማሊያ መውሰዳቸውን ነገር ግን ከሽያጩ ጋር አመርቂ ስራ አለመሰራቱን አምነዋል። ከዚህ ጉዞ ጋር በተያያዘ ቡድኑን የደገፉትን የዲሲ ዩናይትድ ባለ ድርሻ አቶ እዮብ ማሞ፣ ጋዜጠኛ ታምሩ ዓለሙ፣ ጋዜጠኛ አምሃ ፍሰሃና ጋዜጠኛ ሰይፉ ፋንታሁንን አመስግነዋል።
ከቡድኑ ጋር ስለተጓዙትና ስለቀሩት የቡድኑ አባላት ያብራሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው “ሁለት የቡድኑ አባላት
የትጥቅ ኃላፊው አቶ ኃይሉ አውግቾና ፊዚዮቴራፒስት አቶ ሽመልስ ደሳለኝ ከአቅም በላይ በሆነ ሁኔታ ከሆቴል ጠፍተው ከቡድኑ ጋር አልተመለሱም ፓስፖርታቸው ግን በእኛ እጅ ይገኛል በዚህም እንደ ፌዴሬሽን በጣም አዝነናል” ሲሉ ተናግረዋል። ተጨዋቾቹ የሚከፈላቸው አበል ከ100 ዶላር ወደ 50 ተቀንሷል በዚህም የተፈጠረ ቅሬታ አለ የተባሉት አቶ ባህሩ ” የተፈጠረ ችግር የለም ዶላሩም 50 መሆኑ እውነት ነው ወጪ ቀንሱ እየተባልን ነው ከጉዞው አላማ አንጻር 50 ዶላር አበል ተሰጥቷቸው ተቀብለውታል አላማው ለነሱ ለልምድና እድል መፍጠር እንጂ ሌላ አይደለም ተነጋግረን አሳምነናቸው ያደረግነው ስለሆነ አልተቃወሙም ላሳዩንም ትብብርና ድጋፍ እናመሰግናለን” ሲሉ አስረድተዋል።
በመደባደባቸው ከአሜሪካ እንዲመለሱ ስለተደረጉት ሁለቱ ተጨዋቾች ብርሃኑ በቀለና ዮሴፍ ተካኬልኝ የተናገሩት ዋና ስራ አስፈጻሚው ” በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ታሪክ ተጨዋቾች ሲደባደቡ ይሄ ከናይጄሪያ
/ካላባር/ገጠመኝ በኋላ የመጀመሪያ ነው ውሳኔው ለክለቦቻችን ትልቅ መማሪያ ነው ተጨዋቾቹ በተቻለ መጠን መታረም አለባቸው ያገኙትን የመታየት እድላቸውን አበላሽተዋል ፌዴሬሽኑ በቀጣይ የሚወስደው ርምጃም ይኖራል” ሲሉ ተናግረዋል።
ይህን ጉዞ ያስተባበረው ሲ.ጄ. ኒውማን ተቋም ተወካይና የተጨዋቾች ኤጀንት የሆኑት አቶ ዳዊት አርጋው በበኩላቸው “ሚዲያው እያገዘን የመጣበት መንገድ አለ በተቃራኒውም በጎ ያልሆነ ምላሽ አግኝተናል እኛ እናግዝ ስንል ፌዴሬሽኑም ወጣቶችና ስፖርት ቢሮውና ሚዲያውም ልታግዙን ይገባል እናንተ ስራ ላይ የምትሆኑት ኳሱ ሲኖር ነውና አላማችሁ ኳሱ ብቻ ይሁን” ሲሉ ተናግረዋል። እንደ አቶ ዳዊት መግለጫ ” እዚያ የነበሩት ሰዎች ኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አላት? ሱራፌል የኢትዮጵያ ተጨዋች ነው ወይ ? በማለት ባለማመን ሆቴል ድረስ መጥተው አይተውናል እኔም እንደ ተጨዋቾች ወኪልነቴ ተጨዋቾችን ለገበያ ለማቅረብ ተቸግሬያለሁ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
ዋሊያዎቹ የጉያና አቻቸውን 2ለ0 ሲረቱ ከደቀ ዩናይትድን 4ለ2 አሸንፈው መመለሳቸው ይታወሳል።