ላለፉት 3 ወራት በሀዋሳ ከተማ ሲሰጥ የሰነበተዉ የካፍ የC License የእግር ኳስ አሰልጣኝነት ስልጠና በዛሬው እለት በሀዋሳ ከተማ ሴንትራል ሆቴል በተደረገ የመዝጊያ ፕሮግራም ፍፃሜዉን አግኝቷል።
የመዝጊያዉ ፕሮግራም ላይ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍሬዉ አሬራ ፣ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ፣ የሲዳማ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ት/ስ/ዉ/ዳ/ዳይሬክተር አቶ እንግዳ ባዴጎ እና የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ማርቆስ ኤልያስ የተገኙ ሲሆን የእለቱ እንግዳ አቶ ፍሬዉ አሬራ ለሰልጣኞች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን አክለዉም ይሄ ስልጠና በክልላችን እንዲካሄድ የበኩላቸዉን ድርሻ ለተወጡት በተለይ ለሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ትልቅ ምስጋና አሉኝ ያሉ ሲሆን እንዲሁም ለሰልጣኞች ይሄንን ስልጠና ለሰጡት ለኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ እና ለሌሎች ኢንስትራክተሮችም ትልቅ ክብር እና ምስጋና አለኝ በማለት የተናገሩ ሲሆን ሰልጣኞችም ቀጣይ የህይወት ምዕራፋቸዉ የስኬት እንዲሆን እመኛለሁ ብሏል።
- ማሰታውቂያ -
አክለዉ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ አንበሴ አበበ ለሰልጣኞች መልዕክታቸዉን ያስተላለፉ ሲሆን ከሁሉ በማስቀደም የእለቱ የፕሮግራሙ ባለቤቶች እንኳን ደስ አላችሁ ያሉ ሲሆን ይሄንን ስልጠና ስትሰጡልን ለነበራችሁ ለኢንስትራክተሮቻችን ትልቅ ክብር እና ምስጋና ይገባቸዋል ያሉ ሲሆን ሰልጣኞች አሁን ላይ የወሰዳችሁትን ስልጠና በተግባር በማዋል ነገ ላይ በሀገሪቷ አላችሁ የተባላችሁ ትላልቅ አሰልጣኞች እንደምትሆኑ እምነት አለኝ በማለት የተናገሩ ሲሆን በቀጣይ በህይወት ምዕራፋችሁ ላይ የሲዳማ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን አብሯችሁ ነዉ ያለዉ በማለት የተናገረ ሲሆን በቀጣይም የB License ስልጠና ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር በመነጋገር እናዘጋጃለን ብሏል።
እንዲሁም ኤሊት ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን “ይሄ ኮርስ ቢጠናቀቅም ትምህርት ግን ይቀጥላል” በማለት ንግግራቸዉን የጀመሩ ሲሆን የእለቱ ሰልጣኞች ሁሌም አዳዲስ ነገር ለማወቅ የምትጥሩ እና በተሰማራችሁበት በሙሉ በስኬት የምትወጡ ብቁ አሰልጣኞች እንድትሆኑ የአደራ መልዕክቴንም በዚሁ አስተላልፋለሁ ብሏል።
በስተመጨረሻም የእለቱ ሰልጣኞች ለአሰልጣኞቻቸዉ እና ለስልጠናዉ አዘጋጆች ያዘጋጁትን ስጦታ አበርክተዉ በጋራ ፎቶ የመነሳት ፕሮግራም አካሂደዉ የእለቱ ፕሮግራም ተጠናቋል።