“እንቀድሞው ምርጫ ማንም እየተነሳ መግለጫ መስጠት አይችልም”
የኮሚቴው የስነምግባር መመሪያ
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚ ምርጫ ከመካሄዱ በፊት እንደ ቀድሞ የአስመራጭ ኮሚቴ አባላት አንዱ እየተነሳ የፈለገውን የሚናገርበት እንደማይሆን ሚዲያውም እንደሚረዳቸው አስመራጭ ኮሚቴው አስታውቋል።
የአስመራጭ ኮሚቴው ሰብሳቢና የህግ ጠበቃው አቶ ሀይሉ ሞላ፣ አዲስ አበባ ከተማን በምክትል አመራርነት ለበርካታ አመታት የመራው አቶ በለጠ ዘውዴ፣ የመድን እግርኳስ ክለብ ከፍተኛ አመራርና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የይግባኝ ሰሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ መንግስቱ መሃሩ፣ የኢትዮ ኤሌክትሪክ የስፖርት ክለብን ለአመታት የመሩና በሙያቸው የተቋሙ ከፍተኛ አመራር የሆኑት አቶ ኢሳያስ ደንድር በጋራ በሰጡት መግለጫ የትኛውም አባል እየተነሳ መግለጫ መስጠት እንደማይችል አስረግጠው ተናግረዋል።
ኮሚቴው በሰጠው መግለጫ ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ዕጩ ከፌዴሬሽኑ የመመዝገቢያ ፎርም በመውሰድ ሀምሌ 18 ድረስ መመዝገብ እንደሚችሉ ገልጸው ቀኑ እስኪጀመር ድረስ ተዘጋጅተው የሚጠብቁ ተወዳዳሪዎች መኖራቸውን ስለምናውቅ ቀኑ በቂ ነው ሲሉ አስረድተዋል ።”ከሀምሌ 18 እስከ 26 ድረስ ኮሚቴው አጣርቶ ተወዳሪዎቹን ይፋ ካደረገ በኋላ ቅሬታ ያለው ወገን ከሀምሌ 26- ነሀሴ 2/2014 ድረስ ይግባኝ የመጠየቅ መብቱ ይከበራል” ሲል ኮሚቴው አስረድቷል።
- ማሰታውቂያ -
የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ መንግስቱ መሃሩ በበኩላቸው “አስገዳጅና ከውጪ አካል የሚነሳ ጫና ካለ ለመቀበል ዝግጁ አይደለንም ያን ያህል ግን ያሰጋናል ብለን አናስብም” ሲሉ ተናግረዋል። ኮሚቴው
እንደገለጸው ከሁለትና ከሶስት ዘመን በላይ የተወዳዳሩ ሰዎች አሁንም ይችላሉ ወይስ..? ለሚለው ኮሚቴው በሰጠው ምላሽ “ማን ተገቢ ነው ማን አይደለም የሚለው አሁን ሳይሆን በቀጣይ የምንገልጸው ይሆናል በኛ በኩል ትልቅ ሀላፊነት ነው የተቀበልነው
ታሪካችንና ስማችንን ጠብቀን ምርጫው ሀቀኛ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ እንሰራለን” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አቶ ሃይሉ” ምንም ጥርጥር አይግባችሁ ምርጥ የሆነ ምርጫ እንደምናካሂድ አረጋግጥላችኋለው ይሄ ኮሚቴ የሚመራው ግንቦት 7 /2014 የተካሄደው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባኤ ባጸደቀው መመሪያ ደንብ መሠረት ነው ከዚያ ውጪ ማንንም አናስተናግድም ግፊት የሚመጣው የሚገፋ ሲኖር ነው ይህ እንደማይሆን ርግጠኛ ነኝ” ሲሉ በልበ ሙሉነት ተናግረዋል።
“የፌዴሬሽኑ ዋና ጸሀፊ አቶ ባህሩ ፈልገነው ጠርተነው በሚገባ አግዞል እሱንና የጽ/ቤቱ ባልደረቦችንም እናመሠግናለን” ያሉት ዋና ሰብሳቢው “የትግራይ ክልልን በተመለከተ ከተወያየን በኋላ እንደ ክለብ በዚህ ሰዓት እየሰራ ያለውን አሳውቁን ብለን ጽ/ቤቱን ጠይቀናል በቅርቡ ሙሉ ህጋዊ ክለቦችን ዝርዝር አግኝተን የምንሰራ ይሆናል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኮሚቴው ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ በለጠ ዘውዴ አጽንዖት ሰጥቶ እንደተናገረው “ተወዳዳሪዎቹ ደንቡን ሊመለከቱ ይገባል ጫናውን የሚያቀለው አንብበው ተረድተው የሚጠበቅባቸውን አውቀው ቢመጡ ነው በስራችን ማንም ጠምዝዞ የሚያሰራን የለም ሚዲያዎችም ሊያግዙን ይገባል ” ሲሉ ተናግሯል።
ኮሚቴው እንዳስረዳው “ለፕሬዝዳንትም ይሁን ለስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሚወዳደር አንድ ዕጩ የአንድ ክልል ፌዴሬሽንና የአምስት ክለቦችን ድጋፍ ማግኘት አለበት የክለቦቹንና የክልል ፌዴሬሽን ማህተም የታተመባቸው ስድስት ደብዳቤዎች ያስፈልጋል… አንድ ክልል ዕጩ ሲልክ ሁለት ወንድና አንድ ሴት የግድ መሆኑን ቁጥሩን መጨመር እንጂ መቀነስ እንደማይቻል አለበለዚያ ከውድድር ውጪ ይደረጋል” ሲሉ አስረድተዋል።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፕሬዝዳንትና የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ምርጫ የፊታችን ነሀሴ 21 እና 22/2014 ጎንደር ላይ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።