በ2020 የቤጂንግ ኦሎምፒክ ወቅት የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ቡድን በቅድመ ዝግጅት ፤ በውድድር እና በድህረ ውድድር ወቅቶች ላይ አሳዛኝ ክስተቶችን አስተናግዶ ማለፉ ይታወሳል ። ብዙዎችም መለስ ብለው ማስታወስ የማይፈልጉት ኦሎምፒክ ነበር ።
በወቅቱ ለነበሩ ችግሮች ዋነኛው መንስኤ ደግሞ በኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ እና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል የነበረው አለመግባባት ነበር ። በተለይም ሁለቱን ታላላቅ ተቋማት በሚመሩት ሰዎች መካከል የነበረው አለመግባባት በወቅቱ ብዙ መነጋገሪያ ርዕሶችን የፈጠረም ሆኖ አልፏል ።
እነሆ ያ ኦሎምፒክ አልፎ ቀጣዩ የፓሪስ የ2024 ኦሎምፒክ ሊጀመር የ12 ወራት ዕድሜ በቀሩት ወቅት ብዙዎችን የሚያስደስት ዜና ከሰሞኑ ተሰምቷል ።
በአቶ ቢልልኝ መቆያ ታላቅ ጥረት በሁለቱ ተቋማት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች ደረጃ በተለይም ለ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ አሰራርን በተከተለ መልኩ ተደጋግፎ ለመስራት ከቀናት በፊት በሀይሌ ግራንድ ሆቴል የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በዛሬው ዕለትም የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ክብርት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉ በኔዘርላንድስ አምስተርዳም በሚካሄደው የመላው ኢትዮጵያ ፌስቲቫል መክፈቻ ስነ ስርዓት ለመታደም ባቀናችበት ወቅት ቀድመው ተገኝተው የነበሩት የኦሎምፒክ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ዶክተር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ አበባ ይዘው ተቀብለዋታል ።
ይህም የመግባቢያ ስምምነቱ በወረቀት ላይ ብቻ እንዳልሆነ ማሳያ የሆነ አመላካች ተግባር ነው ።
በፓሪሱ ኦሎምፒክ ዝግጅት ዋዜማ ላይ ሆነን ይህም መስማት እና መመልከት እጅግ አስደሳች ነገር ነው። በቶክዮ ኦሎምፒክ አዝኖ በፓሪስስ ብሎ ሲጠይቅ እና ስጋቱን ሲገልፅ ለነበረው የስፖርቱ አፍቃሪም ልብን በሀሴት የሚሞላ ነው ።
ቶክዮ ላይ ተኮራርፈው የነበሩት ሰዎችም ዛሬ ላይ ተቃቅፈው ለአንድ አላማ በአንድ ላይ እንቆማለን በማለት በፓሪስ ኦሎምፒክ እንክሳችኋለን የሚሉን ይመስላል ።