የኢትዮጵያ ፕሪሚየር እንዲህ እንዲያ እያለ እነሆ 6ኛ ሳምንት ላይ ደርሷል። ሊጉ እስካሁን ድረስም ለ5 ሳምንታት በፍጹም ስፖርታዊ ጨዋነት እና እንግዳ ክለብን በመልካም አቀባበል እየተካሄደ ሲሆን ይህም ይበል የሚያስብል ሆኖ እስከ ሊጉ ፍፃሜ መቀጠል አለበት ብለን እናምናለን።
በሊጉ 6ኛ ሳምንት 8ጨዋታዎች በሳምንቱ መጨረሻ የሚካሄዱ ሲሆን አርብ እና እሁድ አንድ አንድ እንዲሁም ቅዳሜ ስድስት ጨዋታዎች የሚደረጉ ይሆናል። ከሚደረጉት ጨዋታዎች መካከል 5ቱ ጨዋታዎች ክልል ላይ ሲደረጉ ቀሪዎቹ 3ጨዋታዎች ደግሞ አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉ ይሆናል። ከነዚህ ጨዋታዎች መካከል ነገ(አርብ) አዲስ አበባ ላይ ሰበታ ከተማ ከወላይታ ድቻ የሚያደርጉትን ጨዋታ በዚህ ቅድመ ዳሰሳ ለእናንተ እንዲስማማ አድርገን አቅርበንላችኋል። መልካም ንባብ።
ጨዋታ: ሰበታ ከተማ ከወላይታ ድቻ
የጨዋታ ቀን: አርብ ታህሳስ 24/2012
የጨዋታ ሰዓት: 9:00
የጨዋታ አርቢትር: ኢንተርናሽናል አርቢትር አማኑኤል ሃ/ስላሴ
የጨዋታ ቦታ: አዲስ አበባ ስታዲየም
- ማሰታውቂያ -
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት ነገ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰበታ ከተማ ከወላይታ ድቻ በሚያደርጉት ጨዋታ 9:00 ላይ የሚጀምር ይሆናል። በ4ኛው ሳምንት የተለያየ ውጤት ይዘው መውጣት የቻሉት እነዚህ ሁለት ቡድኖች የነገውን ጨዋታ በጉጉት እንዲጠብቁት ተገደዋል። ሰበታ ከተማ ድራማዊ ክስተት በታየበት ጨዋታ ፋሲል ከተማን አዲስ አበባ ላይ አስተናግዶ በተጨማሪ ደቂቃዎች ባስቆጠሯቸው ሁለት ግቦች 3-3 አቻ የተለያዩ ሲሆን ወላይታ ድቻ በአንፃሩ በሜዳው በጫላ ተሺታ ብቸኛ ግብ በአዲስ አዳጊው ወልቂጤ ከተማ ሽንፈት ማስተናገዱ ይታወሳል። ይህንንም ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ከውጤት ማጣት ወደ ድል ለመመለስ የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ በተመልካቹ ዘንድ በጉጉት እንዲጠበቅ አስችሎታል።
ሁለቱ ቡድኖች በ5ሳምንት የሊጉ ጉዞ በደረጃ ሰንጠረዡ እኩል ነጥቦችን ሰብስበው በግብ ክፍያ ብቻ ተበላልጠው የተቀመጡ ሲሆን እንግዳው ወላይታ ድቻ በ5 ነጥቦች እና ያለምንም ግብ ክፍያ 12ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ ተጋጣሚው ሰበታ ከተማ በ2የግብ ክፍያ አንሶ በእኩል 5ነጥቦች እና በ2 የግብ እዳ 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ስለሆነም የሚያሸንፈው ቡድን ከተሸናፊው በ3ነጥቦች መራቅ ስለሚችል እና ከወራጅ ቀጠናው ለጊዜውም ቢሆን መራቅ ስለሚችል ከባድ ፉክክር ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
በወላይታ ድቻ በኩል ነጋሽ ታደስ፣ ያሬድ ዳዊት እና ፀጋዬ ብርሀኑ በነገው ጨዋታ በጉዳት የማይሰለፉ ሲሆን በሰበታ ከተማ በኩልም የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኘው አንተነህ ተስፋዬ የማይገባ ሲሆን ከሁለት ሳምንት በፊት ጉዳት ያስተናገደው ባኑ ዲያዋራም ከጉዳቱ አገግሟል ። በነገው ጨዋታ ሊሰለፍ ሊሰለፍ እንደሚችል ይጠበቃል ።