የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት የአ/አ ስታዲየም ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 18ኛ ሳምንት 6 ጨዋታዎች ሁሉም በዚህ ዕለት (ረቡዕ መጋቢት 26/2010ዓ.ም) የሚደረጉ ሲሆን 4ቱ ጨዋታዎች ክልል ላይ እንዲሁም ቀሪዎቹ ሁለቱ ደግሞ አ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረጉ ይሆናል። (መቐለ ከተማ ከቅ/ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ ከወላይታ ድቻ ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ቅ/ጊዮርጊስ እና ወላይታ ድቻ በሳምንቱ መጨረሻ ባለባቸው የአፍሪካ ኮንፈደሬሽን ካፕ ጨዋታ ምክንያት ለሌላ ጊዜ የተላለፈ ሆኗል።)
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከ አርባምንጭ
አ/አ ስታዲየም ላይ ከሚደረጉት ሁለት ጨዋታዎች መካከል በቅድሚያ የሚደረገው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ለሁለቱም ቡድኖች በወሳኝነቱ የሚጠቀስ ነው። ኢትዮ-ኤሌክትሪክም ሆነ አርባምንጭ ከተማ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እጅግ ደካማ እና ወጥ ያልሆነ አቋም እያሳዩ የሚገኙ ሲሆን ይህም ወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲገኙ አስገድዷቸዋል። ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በዘንድሮው ውድድር አሰልጣኝ ብርሀኑ ባየን አሰናብቶ በምትካቸው የቀድሞውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ቢቀጥርም ምንም አይነት የውጤትም ሆነ የጨዋታ መሻሻል ማሳየት አልቻለም። አርባምንጭ ከተማም እንደ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ሁሉ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያምን አሰናብቶ የቀድሞውን የሀድያ ሆሳዕና አሰልጣኝ እዮብ ማለ(አሞካቺን) መቅጠር ቢችልም በወራጅ ቀጠናው ውስጥ ከመዳከር ሊያመልጥ አልቻለም።
- ማሰታውቂያ -
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በ17ኛው ሳምንት አ/አ ስታዲየም በኢትዮጵያ ቡና 91ኛው ደቂቃ ላይ በባፕቲስት ፋዬ በተቆጠረበት ብቸኛ ግብ የተሸነፈ ሲሆን አርባምንጭ ከተማ በአንፃሩ በሜዳው እና በደጋፊው ፊት አሰተናግዶ በእንዳለ ከበደ የ16ኛ ደቂቃ ብቸኛ የፍ.ቅ.ምት ግብ ሲዳማ ቡናን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። ስለሆነም ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ከ16ኛው ሳምንት ሽንፈቱ ለመውጣት እንዲሁም አርባምንጭ ከተማ ደግሞ የ16ኛ ሳምንት ድሉን ለማስጠበቅ እና ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርጉት ጨዋታ በመሆኑ አጓጊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤትና ግንኙነት
ኢትዮ-ኤሌክትሪክ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው 17ጨዋታዎች 3ቱን አሸንፎ በ5 አቻ ወጥቶ በ9 ተሸንፎ 15ግቦችን አስቆጥሮ 26ተቆጥሮበት በ14 ነጥቦች እና በ11 የግብ እዳ የሊጉ ግርጌ ላይ ሲገኝ አርባምንጭ ከተማ በበኩሉ 17ጨዋታዎችን አከናውኖ 4ቱን አሸንፎ በ4 አቻ ወጥቶ በ9 ተሸንፎ 11ግቦችን አስቆጥሮ 23ተቆጥሮበት በ16 ነጥቦች እና በ12 የግብ እዳ 14ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ላይ ተገናኝተው ኢትዮ-ኤሌክትሪክ 2-1 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
በኢትዮ-ኤሌክትሪክ በኩል ምንም አይነት የተሰማ ጉዳት የሌለ ሲሆን በአርባምንጭ በኩል ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተመርጠው የነበሩት እስራኤል ሻጎሌ እና ፅዬን መርዕድ አሁንም ወደ ጨዋታ የማይመለሱ ይሆናል።
ይህንን ጨዋታ አርቢትር አሸብር ሰቦቃ በመሀል ዳኝነት የሚመሩት ሲሆን ጨዋታው 9:00 ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል።
መከላከያ ከኢትዮጵያ ቡና
ዛሬ ከሚደረጉ 6ጨዋታዎች መካከል አ/አ ስታዲየም ላይ የሚደረገው ሁለተኛ ጨዋታ መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና የሚያደርጉት ነው።
ሁለቱ ቡድኖች በጥሩ መነቃቃት ላይ ሆነው የሚያደርጉት ጨዋታ ይሆናል። ኢትዮጵያ ቡና ድንቅ በሚባል ወጥ አቋም እየተጓዘ ሲሆን መከላከያም አሰልጣኝ ሻ/ም ምንያምር ፀጋዬን አሰናብቶ አሰልጣኝ ስዩም አባተን ከቀጠረ በኋላ መሻሻልን በማሳየት ላይ የሚገኝ ቡድን ሆኗል። በመጀመሪያው ዙር በተደረጉ 15ጨዋታዎች 6ግቦችን ብቻ ብቻ ያስቆጠረው የአጥቂ ክፍሉ ባለፉት 2 ጨዋታዎች 3ግቦችን በማስቆጠር መሻሻልን አሳይቷል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንቅ ብቃታቸውን እያሳዩ የሚገኙት አቡበከር ነስሩ እና ሚኪያስ መኮንን ከ20 አመት በታች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ውስጥ በመካተታቸው ለዚህ ጨዋታ አይኖሩም። ይህም ደግሞ የኢትዮጵያ ቡናን የተጫዋች አማራጭ ያሳጣዋል ተብሎ ይጠበቃል።
የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ ዙር ውጤትና ግንኙነት
መከላከያ በዘንድሮው ፕሪሚየር ሊግ ካደረጋቸው 17ጨዋታዎች 4ቱን አሸንፎ በ7 አቻ ወጥቶ በ6 ተሸንፎ 9ግቦችን አስቆጥሮ 15ተቆጥሮበት ከወራጅ ቀጠናው በ5 ነጥቦች ብቻ ርቆ በ19 ነጥቦች እና በ6 የግብ እዳ 11ኛ ደረጃ ላይ ሲገኝ ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ 17ጨዋታዎችን አከናውኖ 7ቱን አሸንፎ በ5 አቻ ወጥቶ በ5 ተሸንፎ 17ግቦችን አስቆጥሮ 13ተቆጥሮበት በ26 ነጥቦች እና በ4 የግብ ክፍያ ከመሪው ደደቢት በ6 ነጥቦች ብቻ ርቆ 6ኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችሏል። ሁለቱ ቡድኖች በመጀመሪያው ዙር የሶስተኛ ሳምንት ጨዋታ አርባምንጭ ላይ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 1-0 በሆነ ጠባብ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
አርቢትር ሃ/የሱስ ባዘዘው የሚመሩት የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ልክ 11:30 ሲል በአ/አ ስታዲየም የሚደረግ ይሆናል።