ከስምንተኛ ሳምንት ጨዋታዎች መካከል ወላይታ ድቻን ከስሁል ሽሬ በሶዶ ሁለገብ ስታዲየም ያገናኘው ጨዋታ በርካታ ሺ የወላይታ ድቻ ደጋፊዎች የክለቡ ሀላፊዎችን ስም እየጠሩ ከባድ ተቃውሞ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት ሲያሰሙ ተስውሏል፡፡ ጨዋታው 9:00 ሰዓት ላይ የጀመረ ሲሆን እንደተለመደው ወላይታ ድቻ 4 3 3 አስተላለፍ ይዞ ወደ ሜዳ ገብቷል፣ በአማካይ ስፍራ ወልዴን ከጉዳት መልስ ያገኘው የገብረክርስቶስ ቢራራ ቡድን፣ እንደሁልግዜው ሁሉ ተገማች አጨዋወት ይዞ ገብቷል፡፡ በርግጥ የወላይታ ድቻ የዛሬው እንቅስቃሴ ውጤቱን ባይገልፅም፡ በመልሶ ማጥቃት የሚጫወት ቡድን ሲያገኝ እንደሚቸገር በዛሬው ጨዋታም ተስተውሏል፡፡
ጨዋታው በተጀመረ በ8ኛውና 9ኛው ደቂቃ ፀጋዬ ብርሀኑ በግምባሩ ገጭቶ የግቡን ቋሚና አግዳሚ ተላኮ የወጣበት ሲሆን፣ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ይጫወቱ የነበሩት ስሁል ሽሬዎች በረዥሙ የተላከ ኳስ የተከላካዮችን መዘናጋት ተጠቅሞ 20 ቁጥሩ ሳሊፊ ፎፎና የመጀመሪያውን ግብ ለባለ እንግዳዎቹ ማስቆጠር ችሏል፡፡
ግብ ያስናገዱት ባለሜዳዎቹ ባዬ ገዛኸኝ በ38ኛው ደቂቃ ከፍፁም ቅጣት ምት ውጭ አክርሮ መቶ ግብ ጠባቂው የያዘበትና በክንፍ እዮብ አለማየሁ አሻምቶ ደጉ ደበበ በግምባሩ ገጭቶ አገባ ሲባል ወደ ውጭ የሰደዳት ኳስ በወ.ዲቻ በኩል በመጀመሪያው 45 የተደረገ ሙከራ ሆኖ በእንግዶቹ መሪነት ዕረፍት ወጥተዋል፡፡
- ማሰታውቂያ -
ከዕረፍት መልስ ባለሜዳዎቹ ተጭነው በመጫወት በተደጋጋሚ የግብ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን፣ በተለይ አማካያቸው እንድሪስ ከገባ በሗላ የወላይታ ድቻ የማጥቃት እንቅስቃሴ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል ችሏል፡፡ ባዬ ገዛኸኝ፣ ፀጋዬ ብርሀኑ፣ እንዲሁም ተስፋዬ አለባቸው ቆቦ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶች በጨዋታው ድንቅ በነበረው የስሁል ሽሬው ግብ ጠባቂ ምንተስኖት አሎ ተይዞባቸዋል፡፡
ስሁል ሽሬዎች በአንፃሩ በጥብቅ መከላከል እንዲሁም በአደገኛ መልሶ ማጥቃት ጨዋታውን አሸንፎ ለመውጣት የገቡ ሲሆን፣ በጨዋታው መጠናቀቂያ የዲቻዎችን መንቀል ተከትሎ በመሬት በረዥሙ የተላከለትን ኳስ የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው የስሁል ሽሬው አጥቂ ሳሊፊ ፎፎና ላይ አንተነህ ጉግሳ በሰራው ጥፋት የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት 64 ቁጥሩ ሀብታሙ ሸዋለም አስቆጥሮ ስሁል ሽሬ ከሜዳ ውጭ 2-0 እንዲያሸንፍ ማድረግ ችሏል፡፡
ጨዋታው በስሁል ሽሬ 2-0 አሸናፊነት የተጠናቀቀ ሲሆን የዲቻ ደጋፊዎች የስሁል ሽሬን ቡድን በአድናቆት በመሸኘት በአንፃሩ የወላይታ ድቻ አስተዳደር ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያሰሙ ተሰምቷል፡፡ የወላይታ ድቻ የወቅቱ አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ በክለቡ የመጨረሻ ጨዋታቸው መሆኑን በተለይ ለሀትሪክ ስፖርት ገልፀዋል፡፡