በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአንደኛ ሳምንት መርሀግብር የሶስተኛ ቀን ውሎ በቀዳሚነት በተደረገው ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና ከድቻ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል ።
በአሰልጣኝ ፀጋዬ ገብረኪዳን በሚመራው ድቻ በቋሚ አሰላለፉ ቢንያም ገነቱ ፤ ያሬድ ዳዊት ፤ አንተነህ ጉግሳ ፤ መልካሙ ቦጋለ ፤ አናጋው ባደግ ፤ በረከት ወልደዮሐንስ ፤ ንጋቱ ገብረስላሴ ፤ ሀብታሙ ንጉሴ ፤ በኃይሉ ተሻገር ፤ ስንታየሁ መንግስቱ እና ቃልኪዳን ዘላለም ሲካተቱ በአሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሚመራው ኢትዮጵያ ቡና በኩል ደግሞ በረከት አማረ ፤ ወልደአማኑኤል ጌቱ ፤ ዘነበ ከድር ፤ ራምኬል ጀምስ ፤ አማኑኤል ዮሐንስ ፤ አብዱልከሪም ወርቁ ፤ አስራት ቱንጆ ፤ መስፍን ታፈሰ ፤ ብሩክ በየነ እና መሐመድኑር ናስር በቋሚ አስራአንድ ተካተዋል ።
በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናዎች በኳስ ቁጥጥሩ የበላይነት ወስደው የተጫወቱበት ሲሆን በወላይታ ድቻ በኩል ወደ ኋላ አፈግፍገው በመከላከል እና የተጋጣሚን የኳስ ፍሰት በሟቋረጥ የሚገኙ ኳሶችን በቶሎ ወደ ፊት በመላክ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ።
- ማሰታውቂያ -
በኢትዮጵያ ቡና በኩል በተለይም በግራ መስመር ባደላ እንቅስቃሴ ወደ ድቻ የግብ ክልል ለመድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ።
በጨዋታው የነበረው የመጀመሪያ የግብ ሙከራ በ8ኛው ደቂቃ ላይ የተመዘገበ ሲሆን ብሩክ በየነ ከሳጥን ውጪ ያደረገው ሙከራ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ከስምንት ደቂቃዎች በኋላ አብዱልከሪም ወርቁ በሳጥን ውስጥ ወደ ግብ የላከው ኳስ በአንተነህ ጉግሳ በዕጅ መነካቱን ተከትሎ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት አዲሱ ፈራሚ ብሩክ በየነ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
በተደራጀ የመከላከል እንቅስቃሴ የቀጠሉት ድቻዎች ወደ ፊት የሚልኳቸው ኳሶች ያን ያህልም ተፅዕኖ መፍጠር ያልቻሉ ሲሆን በተለያዩ አጋጣሚዎች ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ያደረጓቸው ጥረቶችም ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል ።
በ29ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ተክለሚካኤል በግቡ ትይዩ ከርቀት የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ሞክሮ ለጥቂት በግብ ጠባቂው ቢንያም ገነቱ ተመልሶበታል ።
በቀጣዮቹ ደቂቃዎች ላይ ቡናማዎቹ በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ ድቻ የግብ ክልል ለመድረስ ያደረጓቸው ጥረቶች ሳይሰምሩ የመጀመሪያ አጋማሽ ያለ ግብ ሊጠናቀቅ ችሏል ።
በሁለተኛው አጋማሽ ቡናማዎቹ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር የቻሉበት ሲሆን በተለይም ከመስመር በሚነሱ የማጥቃት ሂደቶች ቢንያም ገነቱን ለመፈተን ጥረቶችን አድርገዋል ።
በድቻ በኩልም ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመልሶ ማጥቃት ሂደቶች የደረሱባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለዋል ።
በአጋማሹ ቀዳሚ የግብ ዕድል በ48ኛው ደቂቃ ላይ ስንታየሁ መንግስቱ ከበሀይሉ ተሻገር በረጅም የደረሰውን ኳስ ከራምኬል ጀምስ ጋር አንድ ለአንድ ተፋልሞ ወደ ግብ ያደረገው ሙከራ በቀላሉ በበረከት አማረ ተይዟል ።
ቡናማዎቹ ከመስመሮች ወደ ግብ ክልል በሚልኳቸው ኳሶች እንዲሁም ኳሱን እየገፉም ሆነ በአንድ ሁለት ቅብብሎች ወደ ሳጥኑ መግባት የቻሉባቸው አጋጣሚዎች በርከት ብለው ነበር ። በ56ኛው ደቂቃ ላይ በአንድ ሁለት ቅብብል መስፍን ታፈሰ ከአስራት ቱንጆ የደረሰውን ኳስ ወደ ግብ ሞክሮ በድቻ ተከላካይ ተመልሶ ወጥቶበታል ።
በ66ኛው ደቂቃ ላይም ከግራ መስመር በተነሳ ኳስ መስፍን ታፈሰ ከብሩክ በየነ የደረሰውን ኳስ በአግባቡ ሳይጠቀምበት ቀርቷል ።
ቡናማዎቹ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይም መስፍን ታፈሰ እና አብዱልከሪም ወርቁ ከሳጥን ውጪ ካደረጓቸው ኢላማዎቸውን ያልጠበቁ ኳሶች ውጪ ሌላ ጠንካራ የግብ ዕድል ለመፍጠር አልቻሉም ነበር ።
በመጨረሻም ጨዋታው በሁለቱም በኩል ግብ ሳያስተናግድ 0 ለ 0 በሆነ ውጤት ተጠናቋል ።
በሁለተኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው መስከረም 30 ከቀኑ 10:00 ላይ ኢትዮጵያ ቡና ከሀዋሳ ከተማ የሚጫወት ሲሆን በተከታዩ ቀን 10:00 ላይ ደግሞ ድቻ ፋሲል ከነማን የሚገጥም ይሆናል ።