ጅማ አባቡና አሰልጣኝ ደረጀ በላይ ጋር ተለያይቷል።ገብረመድህን ሀይሌ ደግሞ የክለቡ አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል።
ጅማ አባቡና በባለፈው አመት ከፍተኛ ሊግ የምድቡ የበላይ ሆኖ እንዲያጠናቅቅና ፕሪሚየር ሊጉን እንዲቀላቀል ያደረጉት አሰልጣኝ ደረጀ በላይ በፕሪሚየር ሊጉ ያደረጉት አጀማመር ጥሩ አለመሆኑን ተከትሎ ነው ከክለቡ ጋር የተለያዩት።
- ማሰታውቂያ -
ትናንትና የባለፈው አመት የፕሪሚየር ሊጉ ሻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስን በአዲስ አበባ ስታዲየም የገጠመው ጅማ አባቡና 1 ለ 1 መለያየቱ ይታወቃል።
አሰልጣኙ ከጨዋታው በኋላ በሰጡት መግለጫ በስራቸው ላይ ነፃነት በማጣታቸው ከክለቡ አመራሮች ጋር በመነጋገር ክለቡን ለመልቀቅ ከስምምነት ላይ ደርሻለሁ ብለዋል።
ጅማ አባቡና በፕሪሚየር ሊጉ 12 ጨዋታዎችን አድርጎ በ10 ነጥቦች ወራጅ ቀጠናው ውስጥ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
አዲሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ሀይሌ ለቀጣዮቹ ስድስት ወራት ክለቡን በአሰልጣኝነት ይመራሉ ተብሏል።
አሰልጣኙ በፕሪሚየር ሊጉ 13ኛ ሳምንት በሜዳቸው ወልዲያ ከተማን በሚያስተናግዱበት ጨዋታ ስራቸውን በይፋ ይጀምራሉ።
አሰልጣኝ ገብረ መድህን ሀይሌ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ከግንቦት 1 2008 እስከ መስከረም 30 2009 ድረስ ማሰልጠናቸው ይታወሳል።
ገብረ መድህን በመካከለኛውና የምስራቅ አፍሪካን ዋንጫ ኢትዮጵያ በ1980 ዓመተ ምህረት ከዚምባብዌ ጋር ለፍጻሜ ተጫውታ ዋንጫ ስታነሳ ተሰልፎ ተጫውቷል።ትራንስ ኢትዮጵያ ፤ኢትዮጵያ ቡና ፤ መድህን እና መከላከያን ደግሞ በአሰልጣኝነት መርቷል።