የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የዘንድሮው
የውድድር ጅማሬው ላይ ለክለቡ ደደቢት
በአጥቂው ስፍራ ላይ በመጫወት ጥሩ ብቃቱን
እያሳየ ይገኛል፤ ተጨዋቹ ከችሎታው ባሻገር
ባለው ፍጥነትም ጎሎችን በማስቆጠር የሊጉ
የኮከብ ግብ አግቢነት የመሪነት ደረጃም ላይ
ሊቀመጥ ችሏል፤ ይህ ተጨዋች 7 ቁጥሩ ለባሽና
በብዙዎቹ ዘንድ በችሎታውም ሆነ ባለው ፍጥነት
ከፍተኛ አድናቆት እያተረፈ የሚገኘው አቤል
ያለው ይባላል፤ የደደቢቱ አቤል አሁን ካለው
ብቃቱ ተነስቶም በቀጣይ ጊዜ የኳስ ህይወቱም
በአጭር ጊዜ ውስጥ በችሎታው ክለቡን ብሎም
ሀገሩን ጠቅሞም ራሱንም ለከፍተኛ ዝናና
እውቅና ማብቃትም ዋንኛው ዓላማው መሆኑን
ለሀትሪክ ስፖርት ጋዜጣም አስተያየቱን የሰጠበት
አጋጣሚም ስላለ ከተጨዋቹ ጋር ያደረግነውን
ምልልስ ለእናንተም የምናቀርብላችሁ ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የአሁን
ሰዓት ላይ ካሉት ተጨዋቾች ውስጥ ከእዚህ ቀደም
ባለው ከፍተኛ ፍጥነት የቀድሞውን የአሌክትሪክ
የአጥቂ ስፍራ ተጨዋች ጠንክር አስናቀን
እንድናስታውስ ያደረገን ወጣቱ አጥቂ አቤል
ያለው በሊጉ የውድድር ጅማሬው ላይ ለክለቡ
ደደቢት ግብ ከማስቆጠር ባሻገር የፕሪምየር
ሊጉ ኮከብ ግብ አግቢነትንም እየመራ ሲሆን
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ተመራጭ በመሆንም
የሴካፋው ውድድር ላይ በደቡብ ሱዳን ላይ ሁለት
ግብም ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ የደደቢቱ አጥቂ
በሊጉ ላይ ሲዳማ ቡናን 5-2 ሲረቱ ሶስት ግብ
በማስቆጠርም ከሐዋሳው ዳዊት ፍቃዱ ቀጥሎም
ሀትሪክ የሰራ ተጨዋች ሆኗልና፤ ይህን ተጨዋች
በተለያዩ ጥያቄዎች ዙሪያ አናግረነው የሰጠንን
ምላሽ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
ሀትሪክ፡- ደደቢት ሲዳማ ቡናን 5-2 ሲረታ
ሀትሪክ ለመስራትና ጥሩም ለመንቀሳቀስ ችለሃል፤
- ማሰታውቂያ -
ግጥሚያውን እንዴት አገኘኸው? በድሉስ ምን
ተሰማህ?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሰባተኛ
ሳምንት ጨዋታችንን ቅዳሜ ዕለት ከጠንካራው
ሲዳማ ቡና ጋር በማድረግ ግጥሚያውን በድል
ማጠናቀቃችን በውስጤ ከፍተኛ የሆነ የደስታ
ስሜት ነው እንዲፈጠርብኝ ያደረገው፤ በጨዋታው
ያን ዕለት ከእኛ ድል አድራጊነት ባሻገር ሶስት
የድል ጎሎችንም በማስቆጠር ሀትሪክ ለመስራትና
ጥሩም ለመንቀሳቀስም ስለቻልኩ የደስታዬን
መጠን የበለጠ እጥፍ ድርብም አድርጎልኝ ምሽቱን
በጥሩ ሁኔታ ላሳልፍ ችያለው፤ ይህንን ብቃቴን
ወደፊትም ሌሎች በርካታ ተጨማሪ ግቦችንም
ዳግም በማስቆጠር ማሳየትም እፈልጋለሁ፡፡
ሀትሪክ፡- ደደቢት ሲዳማ ቡናን በሰፊ ግብ
ሲያሸንፍ ዋናው ጥንካሬው ምን ነበር? የእነሱን
አቋምስ እንዴት አገኘኸው?
አቤል፡-የሲዳማ ቡናን በ5-2 ሰፊ ግብ
ለመርታት የቻልንበት ዋንኛው ጠንካራ ጎናችን
ያን እለት ሁላችንም እንደ ቡድን በማጥቃቱ በኩል
ጥሩ ለመንቀሳቀስ ስለቻልንና በእንቅስቃሴው
ረገድም እንፈጥን ስለነበርና የእኔም ያን ዕለት ላይ
የነበረኝ አቋም ከእስከዛሬው ብቃቴ በአቻነቱ ወደር
የማላገኝለትም ስለነበር ጨዋታው ላይ ያን የመሰለ
ጥሩ ውጤትን ሊያስገኝልን ችሏል፡፡ የሲዳማ ቡና
አቋምን በተመለከተ ያን እለት እኛ ከእነሱ በተሻለ
መልኩ በመቅረብ በሰፋ ግብ እናሸንፋቸው እንጂ
ከተወሰኑ ክፍተቶቻቸው በስተቀር ደካማ የሚባሉ
አይደሉም፡፡
ሀትሪክ፡- ከወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲ
ክለብ ላይ የሊጉን መሪነት በመረከብ አሁን
ውድድሩን እየመራችሁ ነው፤ ዘንድሮ የምትጫ
ወቱት የሊጉ ጠንካራ ተፎካካሪ ለመሆን ነው
ወይንስ ዋንጫውን ለማንሳት?
አቤል፡- የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የሊጉ
ተሳትፎ ውስጥ ከገባ ጊዜ አንስቶ ሁሌም
የሚጫወተው የውድድሩ ጠንካራ ተፎካካሪ
ለመሆን ሳይሆን ዋንጫውን ለማንሳት ነው፤
ክለቡ በእዚያን መልኩ ተጫውቶም ወደ ሊጉ
በገባ አጭር ዓመታት ጊዜ ውስጥ በ2005
ዋንጫ ማንሳቱ ይታወቃል፤ የጥሎ ማለፍ
ዋንጫንም ሊያገኝ ችሏል፤ ስለዚህም አሁንም
ዋንጫን የማምጣት ትልቅ አቅሙ ስላለን በሊጉ
የምንሳተፈው ይህንን እልም ለማሳካት ነው፡፡
ሀትሪክ፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የኮከብ
ግብ አግቢነቱን በ4 ግብ ከኤሌክትሪኩ አልሀሰን
ካሉሻ ጋር በጋራ እየመራህ ነው፤ ዘንድሮ የሊጉ
ኮከብ ግብ አግቢ የምትሆን ይመስልሃል?
አቤል፡- የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ
ከወዲሁ 4 ግቦችን በማስቆጠር ያለኝ የውድድር
ጅማሬ ጥሩና የሚያበረታታኝ ከመሆኑ አኳያ
የዘንድሮው ዋነኛ ዓላማዬ ሁለት ናቸው፤
የመጀመሪያው የሀገሪቱን የሊግ ዋንጫ ማንሳት
ከመፈለጌ ባሻገር የኮከብ ግብ አግቢነቱንም ክብር
ለማግኘትም የምፈልግ ተጨዋች ስለሆንኩ
እነዚህን ህልሞቼን እውን ለማድረግ ጠንክሬ
ነው የምሰራው፤ ስኬቶቹን የማሳካው ያህልም
ነው የሚሰማኝ፡፡
ሀትሪክ፡- ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም
ተመርጠህ ግብ ማስቆጠር ችለሃል፤ አሁንም
ለደደቢት ግብ እያስቆጠርክና ጥሩ እውቅናንም
እያገኘህ መጥተሃል፤ ይሄን ስኬትና ዝና በአጭር
ጊዜ ውስጥ አገኛለሁ ብለህ ጠብቀህ ነበር?
በፍጥነት ከመቀላቀሌ አኳያ በብሄራዊ ቡድን ደረጃ
ለመመረጥና ብሎም ደግሞ ለሀገሬና ለክለቤም
ደደቢት ተሰልፌ በመጫወት ከወዲሁ ጎሎችን
በማስቆጠር በአጭር ጊዜ ውስጥ በአበረታች
መልኩ እንዲህ ያለ እውቅናና ዝናን አገኛለሁ
የሚል እምነት ፈፅሞ አልነበረኝም፤ አሁን ግን
ብዙዎቹ ስለእኔ እያወሩ እንድበረታታ እያደረጉኝ
ነው፤ ያም ሆኖ ግን የደደቢትና የኢትዮጵያ
ብሄራዊ ቡድን ላይ አሁን እያገኘሁት ያለው
አድናቆትና እውቅናም እኔን የሚያስኮፍሰኝ
ሳይሆን ሌሎች ጠንካራ ስራዎችን እንድሰራና
እንድዘጋጅ የሚያደርገኝ ስለሆነ ለእዚያም ነው
ሁሌም የምዘጋጀው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳስን መጫወት
የጀመርክበት ሂደት ምን መልክ ያለው ነው?
አቤል፡- የእግር ኳስን መጫወት የጀመርኩት
እንደአብዛኛው ኢትዮጵያዊ በተወለድኩበት
የአዲስ አበባ የ22 ማዞሪያ አካባቢ ልጅ ሆኜ
በመጫወት ነው፤ ለኳስ ጥልቅ ፍቅርም
ስለነበረኝ ከሕፃንነቴ አንስቶም እየተጫወትኩ
በማደግ ወደ ክለብ ደረጃ ልገባ ችያለው፤ በኋላም
በኳሱ ጠንክሬ እየሰራው በመምጣት በአጭር
ጊዜ ውስጥ ለአሁኑ ጥሩና አበረታች በሚባል
ደረጃ ልገኝ ችያለው፡፡
ሀትሪክ፡- የእግር ኳሱን ስትጫ ወት የአንተ
ተምሳሌት ወይንም ደግሞ አርአያ ያደረግከው
ተጨዋች ማን ነው?
አቤል፡- የእግር ኳስን በማናቸውም ደረጃ
ላይ ሆነህ መጫወት ስትጀምር የራስህ የሆኑ
የምታደንቃቸውና ተምሳሌት የምታደርጋቸው
ተጨዋቾች አሉ፤ በእዚሁም መሰረት እኔም
ኳስን ስጫወት የራሴ የሆነኝ ሞዴል ወይንም
ደግሞ ተምሳሌት የሆነኝ ተጨዋች ጌታነህ
ከበደ ነው፤ ጌታነህ በሀገራችን ውስጥ ከሚገኙ
ምርጥ አጥቂዎች መካከል በችሎታው ቀዳሚ
ስፈፍራ ላይ የማስቀምጠውና የማደንቀው
ተጨዋች ነው፤ የአጥቂ ስፍራው ላይ ያለው
የግብ አነፍናፊነትና የቦታ አጠባበቁም በጣም
ጥሩም ነውና እሱን ነው አርኃዬ ያደረግኩት፡
፡
ሀትሪክ፡- ከደደቢት ክለብ ውጪ በየትኖቹ
ቡድኖች ውስጥ ተጫውተህ አሳልፈሃል?
ስለክለቦቹ ቆይታህስ ምን ትላለህ?
አቤል፡- የደደቢት ክለብ ውስጥ
ገብቼ ከመጫወቴ በፊት የእግር ኳስን
የተጫወትኩባቸው ቡድኖች የሐረር ሲቲና
የፋሲል ከተማ ክለቦች ናቸው፤ በእነዚህ
ቡድኖች ቆይታዬም ተስፋ ሰጪ የሆኑ
ነገሮችን በራሴ ላይ ለመመልከት ችያለሁ፤
የእነሱ ክለቦች ቆይታዬም ነው አሁን ላይ
ለምገኝበትም አበረታች የሆነ ብቃት ላይ
እንድገኝ ያስቻለኝና ይህንን ቆይታዬን በጥሩ
መልኩም ነው መግለፅ የምፈልገው፡፡
ሀትሪክ፡-የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ላይ
እንደተመለከትንህ በጣም ፈጣኑ ተጨዋች
ነህ፤ ፍጥነቱ ከየት ነው የመጣው?
አቤል፡- የደደቢት ክለብ ውስጥ ኳስን
ስጫወት አሁን ያለኝ ፍጥነት ሊመጣና ሊገኝ
የቻለው ከልጅነቴ አንስቶ በተፈጥሮ አብሮኝ
የመጣ ነው፤ በቀጣይ ጊዜም ተጨማሪ
የሆኑ ልምምዶችን ስሰራ ከእዚህ የበለጠም
ልፈጥን የምችልበት እድሉ ይኖረኛል ብዬም
አስባለው፡፡
ሀትሪክ፡- በመጨረሻ…
አቤል፡- በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ
የአጭር ጊዜ የውድድሩ ተሳትፎዬ ከወዲሁ
ለክለቤም ሆነ ለሀገሬ ጎሎችን በማስቆጠር
የአሁን ሰዓት ላይ አበረታች በሚባል ብቃት
ላይ መገኘት መቻሌን በጣም እየወደድኩት
ነው፤ በችሎታዬ ከእዚህም ከፍ ባለ
ስፍራ ላይ በመድረስም ክለቤን ለውጤት
ለማብቃትና ራሴንም ለከፍተኛ እውቅናም
ማብቃት እፈልጋለሁና ለእዚያ ሁሌም
በርትቼ እሰራለው፤ ከእዚያ ውጪ የአሁን
ሰዓት ላይ ለምገኝበት ደረጃ ከእኔ ጎን ሆነው
እየረዱኝ ላሉት የቡድናችን ተጨዋቾች
የክለባችን አመራሮች ደጋፊዎቻችንና እኔን
አሰልጥነው ላለፉና እያሰለጠኑኝ ላሉት
አሰልጣኞችና ለቤተሰቦቼ ከፍተኛ ምስጋናን
ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡