በሊጉ የ24ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ ከቀን 10:00 ጀምሮ የተደረገው የጅማ አባጅፋር እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታ ከዕረፍት መልስ ጋቶች ፓኖም ባስቆጠረው ብቸኛ የቅጣት ምት ግብ ፈረሰኞቹ ወደ ድል ተመልሰዋል ።
ጅማ አባጅፋሮች በ23ኛው ሳምንት በሰበታ ከተማ በተረቱበት ጨዋታ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ የአብስራ ሙሉጌታ ፤ አስጨናቂ ፀጋዬ ፤ ቦና አሊ እና ዱላ ሙላቱን በተስፋዬ መላኩ ፤ አድናን ረሻድ ፤ ሙሴ ከበላ እና ዳዊት እስጢፋኖስ ምትክ ሲያሰልፉ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ከወላይታ ድቻ ነጥብ በተጋሩበት ጨዋታ ከነበረው ምርጥ 11 ሁለት ለውጦችን በማድረግ በደስታ ደሙ እና ከነአን ማርክህ ምትክ ሱሌማን ሀሚድን እና ሀይደር ሸረፋን በማስገባት ጨዋታውን ጀምረዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ቀዝቀዝ ያለ እንቅስቃሴን ያስመለከን ነበር ። በአጋማሹ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይም ከራሳቸው የሜዳ ክፍል በረጅም ወደ ተጋጣሚ ሳጥን አካባቢ በሚጣሉ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን አድርገዋል ። በጅማ አባጅፋር በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስተ ተጫዋቾችን የሚነጥቋቸውን ኳሶች በፈጣን ወደ ፊት መስመር ላሉ ተጫዋቾቻው በማድረስ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ።

በፈረሰኞቹ በኩል በተለይም የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ ለአማኑኤል ገብረሚካኤል በረጅም የሚደርሱት ኳሶች እምብዛም ውጤታማ የነበሩ አይደሉም ። በጨዋታው የመጀመሪያው የግብ ዕድል 17ኛው ደቂቃ የተደረገ ሲሆን አማኑኤል ገብረሚካኤል ከፍሪምፖንግ ሜንሱ በረጅም የደረሰውን ኳስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተከትሎ ከፍ አድርጎ ወደ ግብ የላከው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ቀርቷል ።
ከአንድ ደቂቃ በኋላ ደግሞ በጅማ አባጅፋር በኩል ሱራፌል ዐወል ከቀኝ መስመር አቅጣጫ የተገኘውን የቅጣት ምት ወደ ግብ ክልል አሻግሮ መሀመድኑር ናስር በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል ።
ከውሀ እረፍት መልስ ጅማ አባጅፋሮች ቀድሞ ከነበራቸው እንቅስቃሴ በተሻለ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል መድረስ የቻሉባቸውን አጋጣሚዎች መፍጠር ችለው ነበር ።

በ35ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት ያጋጠመው ቡልቻ ሹራ ጨዋታውን መቀጠል ባለመቻሉ በዳግማዊ አርአያ ተቀይሮ ወጥቷል ። የተጫዋቹ መጎዳት ከዚህ ቀደም እስማኤል ኦሮ አጎሮ ፤ አቤል ያለው ፤ አዲስ ግደይን እና ከነአን ማርክነህ የመሳሰሉ የማጥቃት ባህሪ ያላቸውን ተጫዋቾች በጉዳት ላጣው የዘሪሁን ሸንገታ ቡድን ሌላ የራስ ምታት ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል ።
በ42ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ ከማዕዘን ያሻገረው እና በአማኑኤል ገብረሚካኤል ተጨርፎ ምኞት አግኝቶ ወደ ግብ ሞክሮ ከግቡ አናት በላይ የወጣው ሙከራ የአጋማሹ የመጨረሻ የግብ ሙከራ ሆኖ በ0 – 0 ውጤት ወደ እረፍት አምርተዋል ።
የሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ስድስት ደቂቃዎች በኋላ ፍሪምፕንግ ሜንሱ በርቀት ለቸርነት ጉግሳ የላከለትን ኳስ የጅማ አባጅፋሩ ግብ ጠባቂ አላዛር ማርቆስ ከሳጥን ውጪ በአጅ በመንካቱ የዕለቱ የመሀል ዳኛ ተከተል ተሾመ በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ አሰናብተውታል ። ሌላኛው ግብ ጠባቂ ለይኩን ነጋሽም ቦና አሊን ቀይሮ ወደ ሜዳ ገብቷል ። በሁነቱ የተሰጠውን የቅጣት ምት 15 ቁጥር ለባሹ ጋቶች ፓኖም 57ኛው ደቂቃ ላይ መቶ ከመረብ ላይ አሳርፎታል ።

ከግቡ መቆጠር በኋላ ጅማ አባጅፋሮች በተወሰነ መልኩ በአንድ ሁለት ቅበብሎች ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ የግብ ክልል ለመድረስ ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን ወደ ፊት ሲሄዱ ጥለዋቸው የሚሄዱ ክፍተቶችን በፈጣን እንቅስቃሴ ለመጠቀም ፈረሰኞቹ ሙከራዎችን አድርገዋል ።
64ኛው ደቂቃ ላይ የጅማአባጅፋሩ ተጫዋች አስጨናቂ ፀጋዬ በጉዳት ምክንያት ጨዋታውን አቋርጦ የወጣ ሲሆን በምትኩም እዩብ አለማየሁ ተቀይሮ ገብቷል ።
68ኛው ደቂቃ ላይ መሀመድኑር ናስር ፤ እዩብ አለማየሁ እና ዱላ ሙላቱ ያደረጉት ቅብብል በሳጥኑ የግራ አቅጣጫ ገብቶ በመጨረሻም በመሀመድኑር ናስር አማካኝነት ወደ ግብ ተሞክሮ የነበረ ቢሆንም ቻርለስ ሉክዋጎ ኳሱን መልሶታል ።

ወደ መጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ፈረሰኞቹ ኳሱን ተቆጣጥረው በመጫወት ሌላ ግብ ለማከል ጥረቶችን ያደረጉ ሲሆን 83ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር ካሻገረውና በአማኑኤል ገብረሚካኤል ተገጭቶ ከግቡ አናት በላይ ከወጣው ኳስ ውጪ ግን ሌላ የግብ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ነበር ።
በጅማ አባጅፋር በኩልም ከመሀመድኑር ናስር ሙከራ ሌላ 86ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይሮ የገባው እዮብ አለማየሁ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የመታው ኳስ በቻርለስ ሉክዋጎ በቀላሉ ተይዟል ።
በመጨረሻም ቅዱስ ጊዮርጊስ 1 ጅማ አባጅፋር 0 ሆኖ ጨዋታው ተጠናቋል ።
ውጤቱን ተከትሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥቡን 54 በማድረስ ከተከታዩ ያለውን ልዩነት ወደ 11 ከፍ ሲያደርግ ጅማ አባጅፋር በበኩሉ በነበረበት 19 ነጥብ እና 15ኛ ደረጃ ለመቆየት ተገዷል ።

በ25ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በመጪው ግንቦት 13 ( ቅዳሜ ) ረፋድ 4:00 ጀምሮ ጅማ አባጅፋር አዲስ አበባ ከተማን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ግንቦት 14 ( ዕሁድ ) በተጠባቂው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፋሲል ከተማን የሚገጥም ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ