በቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ25ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ውሎ ቀዳሚ ጨዋታ አዳማ ከተማን ከሰበታ ከተማ አገናኝቶ ዋና አሰልጣኙን ካሰናበተ በኋላ የመጀመሪያ ጨዋታውን ያደረገወ እና ለረጅም ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች የተጫወተው አዳማ ከተማ ሶስት ግቦችን በማስቆጠር አሸንፏል ።
አዳማ ከተማዎች በ24ኛ ሳምንት ጨዋታ በባህርዳር ከተማ ሲረቱ ከነበረው የመጀመሪያ አሰላለፍ አራት ለውጦችን በማድረግ የገቡ ሲሆን አዲስ ተስፋዬ ፤ ዮናስ ገረመው ፤ ፀጋአብ ዮሴፍ እና አቡበከር ወንድሙን በቶማስ ስምረቱ ፤ ዮሴፍ ዮሀንስ ፤ ታደለ መንገሳ እና አሜ መሀመድ ምትክ ሲያሰልፉ በሰበታ ከተማ በኩል ደግሞ በሳምንቱ ሰበታ ከተማን በረቱበት ጨዋታ በነበረው ምርጥ 11 ላይ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ጨዋታውን ጀምረዋል ።
የጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃ እንቅስቃሴዎች በመሀል ላይ ተገድበው የነበሩ ሲሆን የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀው የግብ ዕድልም ወደ ግብነት የተቀየረ ነበር ። በ10ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘውን የማዕዘን ምት ኳስ አዳማ ከተማዎች እዛው ጀምረውት አቡበከር ወንድሙ ከቀኝ መስመር አቅጣጫ ወደ መሀል የቀነሰውን በግቡ ትይዩ የነበረው አዲስ ተስፋዬ አስቆጥሮ አዳማ ከተማን መሪ ማድረግ ችሏል ።

ከግቡ በኋላም አዳማ ከተማዎች በተሻለ ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል በመድረስ የተከላካይ መስመሩን መፈትን ችለው ነበር ። በሰበታ ከተማ በኩል ኳሱነሰ ይዘው በአነሰድ ሁለት ቅብብል ወደ ተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ለመድረስ ጥረት በሚያደርጉበት ወቅትም ኳሶችን ነጥቀው በፈጣን መልሶ ማጥቃት የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረቶችን ማድረግ ችለዋል ።
በአዳማ ከተማ በኩል የቡድኑ አምበልና ወሳኝ ተጫዋች ዳዋ ሆቴሳ በቃላት ልውውጥ ምክንያት በቀጥታ የቀይ ካርድ ከሜዳ ተሰናብቷል ።
ሰበታ ከተማዎች ከውሀ እረፍት መልስ በጥሩ ቅብብሎች ወደ አዳማ ከተማ ሳጥን ለመድረስ የሚያደርጓቸው ሙከራዎች በተደጋጋሚ በአዳማ ከተማ ተጫዋቾች ይነጠቁ የነበረ ሲሆን ከተከላካዮች ጀርባ የሚጥሏቸው ኳሶችም በተደጋጋሚ ከጨዋታ ውጪ በመሆን ሳኩባ ካማራን የፈተነ አንድም የግብ ሙከራ ሳያደርጉ የመጀመሪያውን አጋማሽ ለማጠናቀቅ ተገደዋል ።
ሁለተኛውን አጋማሽ ሰበታ ከተማዎች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል በመቅረብ የጀመሩት ቢሆንም ወደ ግብ ጠባቂውን መፈተን የቻሉ ሙከራዎችን ግን ማድረግ አልቻሉም ነበር ። በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች በፈጣን ሽግግር ወደ ሰበታ ከተማ የግብ ክልል የሚዳደርሷቸው ኳሶች እና የነበራቸው ጥሩ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ አንድ ተጫዋች ጎድሎባቸው የሚጫወቱ አይመስሉም ነበር ።
አዳማ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴዎች ደጋግመው የሰበታ ከተማን የኋላ ክፍል ማስጨነቅ የቻሉ ሲሆን በተለይም በሁለቱ መስመሮች በኩል ሰብረው ለመግባት የሚያደርጓቸው ጥረቶች የሚደነቁ ነበሩ ።
ለረጅም ደቂቃዎች የግብ ሙከራን ሳያስመለክተን የቆየው ጨዋታ በ80ኛው ደቂቃ ላይ ሁለተኛ ግብ አስተናግዷል ። አዳማ ከተማዎች ከቀኝ መስመር ወደ ሳጥን ይዘው የገቡት ኳስ ሲመለስ አግኝቶ ዮናስ ገረመው በግንባር ገጭቶ ወደ ግብ የላከው ኳስ በዱሬሳ ሹቢሳ በእጅ በመነካቱ የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት ደስታ ዮሀንስ አስቆጥሮታል ።

የግብ ሙከራዎችን ለማድረግ አይናፋር ሆነው የቆዩት ሰበታ ከተማዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ላይ ሶስት ለግብ የቀረቡ የግብ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል ።
በ84ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳሊሶ ከዱሬሳ ሹቢሳ የተሻገረለትን ኳስ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የሞከረውን ኳስ ሚሊዮን ሰለሞን ተደርቦ አውጥቶታል ። ከአንድ ደቂቃ በኋላም አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ ከሳጥኑ ጫፍ ላይ ወደ ግብ የሞከረው ኳስ በሳኩባ ካማራ ተመልሷል ።
በ90ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ደስታ ዮሀንስ የነጠቀውን ኳስ ወደ ሳጥን ይዞ ገብቶ ያቀበለውን ኳስ ዮናስ ገረመው ወደ ግብነት ቀይሮ የአዳማ ከተማን የግብ መጠን ወደ 3 ከፍ አድርጎታል ።

ከአንድ ደቂቃ በኋላም አዳማ ከተማዎች በፈጣን እንቅስቃሴ በግራ መስመር አቅጣጫ ይዘው የገቡትን ኳስ በደስታ ዮሀንስ አቀባይነት እና በአሜ መሀመድ ጨራሽነች ወደ ግብ መቀየር ቢችሉም የመስመር ዳኛው በተሳሳተ ውሳኔ ከጨዋታ ውጪ ብለውታል ።
በተጨማሪ ደቂቃዎች ላይ ዴሪክ ንስባምቢ ወደ ግብ የሞከረው ኢላማውን የጠበቀውነ ኳስ ግብ ጠባቂው ሳኩባ ካማራ ተቆጣጥሮታል ።
በመጨረሻም አዳማ ከተማ 3 – 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል ።
ውጤቱን ተከትሎ አዳማ ከተማ ነጥቡን 30 በማድረስ ወደ 8ኛ ከፍ ሲል ሰበታ ከተማ በበኩሉ የሊጉን ግርጌ ይዞ ለመቆየት ተገዷል ።
በ26ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሰኔ 5 ( ዕሁድ ) ረፋድ 4:00 ላይ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን ሲገጥም በተከታዩ ቀን ሰኔ 6 ( ሰኞ ) 10:00 ላይ ሰበታ ከተማ ከፋሲል ከነማ የሚጫወት ይሆናል ።
አስተያየት ይስጡ