➯ ኢትዮጵያ ቡና እና ቅዱስ ጊዮርጊስ የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል
ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 2014 በ17ኛ ሳምንት በተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች 5 በመሸናነፍ ሶስቱ በአቻ ውጤት ተጠናቀዋል። በሳምንቱ 13 ጎሎች በ12 ጨዋታዎች የተቆጠሩ ሲሆን 26 ቢጫ ካርድ እና 2 ቀይ ካርድ በተጫዋቾች እና የክለብ አመራሮች ላይ የተመዘዙ ናቸው።
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ውድድር አመራርና ስነ-ስርዓት ኮሚቴ ቅዳሜ ሚያዝያ 1 2014 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ የተደረጉ ፕሪሚየር ሊግ ግጥሚያዎች ከዳኞች እና ከታዛቢዎች የቀረቡለትን የዲሲፕሊን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ በተጫዋቾች፣ በክለብ አመራሮች እና ክለቦች ላይ የተለያዩ ውሳኔዎችን ሰጥቷል።
በተጫዋቾች እንድሪስ ሰይድ (ወላይታ ድቻ) በከባድ የአጨዋወት ጥፋት ከጨዋታ ሜዳ የተወገደ ስለመሆኑ ሪፖርት የቀረበበት በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ መሰረት 3 ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 3000 /ሶስት ሺ/ እንዲከፍል፥ ወንድማገኝ ሐይሉ(ሃዋሳ ከተማ) እና መሳይ ጳውሎስ(ድሬደዋ ከተማ) በተለያዩ 5 ጨዋታዎች የቢጫ ማስጠንቅቂያ ካርድ ስለተመለከቱ ቀጣይ 1 ጨዋታ እንዲታገዱና በተጨማሪ የገንዘብ ቅጣት ብር 1500 /አንድ ሺ አምስት መቶ/ እንዲከፍሉ ወስኗል።
- ማሰታውቂያ -
በክለቦች ደረጃ ኢትዮጵያ ቡና ክለቡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በነበረው ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የተጋጣሚ ቡድን አመራሮችን ስለመሳደባቸው እና ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደሜዳ ስለመወርወራቸው እንዲሁም 42 ወንበሮች የተቆረጡ፣የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት ቀርቦበታል። ስለሆነም የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋትና ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ሁኔታ ክለቡ መቀጣቱና ደጋፊዎቹም ሊታረሙ አለመቻላቸውን ታሳቢ በመድረግ ክለቡ በኢ.እ.ፌ ዲሲፕሊን መመሪያ ክፍል 3 ምዕራፍ 3 አንቀፅ 66 በተቁ 4(ሀ) መሰረት ብር 75000/ሰባ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
ቅዱስ ጊዮርጊስም የክለቡ ደጋፊዎች ቁርጥራጭ ወንበሮችን ወደሜዳ ስለመወርወራቸው እንዲሁም 34 ወንበሮች የተቆረጡ፣የተሰነጠቁ ወይም የተነቀሉ ስለመሆናቸው ሪፖርት የቀረበበት ብር 25000/ሃያ አምስት ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል። አዳማ ከተማም ክለቡ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር በነበረው የ17ኛ ሳምንት እግርኳስ ጨዋታ የክለቡ ደጋፊዎች የእለቱን ዳኛና የተጋጣሚ ቡድን አሰልጣኝን አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት የቀረበበት የክለቡ ደጋፊዎች ለፈፀሙት ጥፋት ብር 50000/ሃምሳ ሺህ/ እንዲከፍል ተወስኗል።
በክለብ አመራሮች አቶ ወንድሙ ሳሙኤል – ወላይታ ድቻ(የቡድን መሪ) ክለቡ ከ ሃዋሳ ከተማ ጋር በነበረው ጨዋታ የእለቱን ዳኛ በቃልና በምልክት አፀያፊ ስደብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት ስለቀረበባቸው 5000/አምስት ሺህ/ እንዲከፍል እና 6 ጨዋታ እንዲታገዱ ተወስኗል።
በተገቢነት ክስ ላይ በተላለፈ ውሳኔን በተመለከተ የውድድርና ስነስርዓት ኮሚቴ ወልቂጤ ከተማ ከፋሲል ከነማ ባደረጉት ጨዋታ የፋሲል ከነማ ቡድን በወልቂጤ ተጫዋቾች ላይ ባቀረበው የተገቢነት ክስ ምክንያት ውጤቱ ለጊዜው እንዳይፀድቅና ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማብራሪያ እንዲጠየቅበት መወሰኑን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማህበር ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።


